የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማሕበራት እና ተቋማት እንዲሆኑ ሂደቱ ጠንካራ መሰረት ጥሏል – የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማሕበራት እና ተቋማት እንዲሆኑ ሂደቱ ጠንካራ መሰረት መጣሉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የሀገራዊ ምክክር ባለቤት ማን ነው? በሚል ርዕስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በዚህም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማሕበራት እና ተቋማት እንዲሆኑ የእስካሁኑ ሂደት ጠንካራ መሰረት ጥሏል ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች፣ በመንግስት እና በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ለተፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶች መፍትሔን በውይይት ለማበጀት የሚከናወን ሂደት ነው ብሏል፡፡

ሂደቱ በሀሳብ መሪዎች፣ በፖለቲካ ከዋኞች እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባትን ማስፍን ያስችላል ተብሎ እንደሚታመንም ገልጿል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደትን የሚያስተባብር እና ሂደቱን በበላይነት የሚመራ ገለልተኛ አካል መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የሂደቱ ባለቤት ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ አስፈላጊ መሆኑንም አንስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቋቋመበት አዋጅ መግቢያ ላይ ሀገራዊ ምክክሮች ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ከሚያስችሏቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክሮቹን የሚያመቻቸውና የሚመራው አካል ብቃት እና ገለልተኝነት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚከናወነውን የምክክር ሂደት ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ አካል መምራቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና ለዚህም መንግስት ተነሳሽነቱን በመውሰድ ከሕዝብ በሚሰበሰብ ሙዓለ-ንዋይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አቋቁሟል ብሏል፡፡

ይህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግስት፣ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ የማሕበረሰብ መሪዎች የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ነው ያለው፡፡

ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን ግንባር ቀደም መርሆዎቹ በማድረግ የተለያዩ ተሳታፊዎችን በውክልና በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ እና አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲያሰባስብ የብዙ አካላትን ተሳትፎ እና ውክልና በማረጋገጥ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባልም ነው ያለው ኮሚሽኑ በመልዕክቱ፡፡

ሂደቱ ሕዝብ ከሚገኝበት የመጀመሪያው ወይም ቀዳሚ አሃድ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፤ በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ማህበራትን፣ መንግስታዊ እና መንግሰታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪክ ማህበራትን ያሳተፈ እንዲሆን ተቀርጿል ብሏል።

ያንን ተከትሎ የሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማሕበራት እና ተቋማት እንዲሆኑ ሂደቱ ጠንካራ መሰረት ጥሏል ሲልም አስታውቋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሊያሳካው የቆመለት ዓላማ አለው ያለው ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱ የተለያዩ ውጤቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሊያስገኝ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ጥቅል ዓላማው ሀገራዊ መግባባትን ማስፈን ነው ብሏል፡፡

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤቶች ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማመንጨት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ሲልም ገልጿል፡፡

የዚህ ዋነኛ ተጠቃሚም የሀገራችን ኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያለው ኮሚሽኑ ይህም ሕዝቡን የሀገራዊ ምክክሩ ግንባር ቀደም ባለቤት እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያለው፡፡

በርካታ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ እየተሳተፉ ባለቤትነታቸውን ሲያዳብሩ ሂደቱም ምሉዕ እየሆነ የተለያዩ ፈተናዎችን መቋቋም ይችላል ብሏል በመልዕክቱ፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ በሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል የሚልን ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ማህበር ወይም ተቋም ድምፅ(ሀሳብ) ለመስማት ብሎም ለማካተት እንደሚሰራማስታወቁን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡፡፡

ከሚሽኑ ሁሉም አካል በባለቤትነት መንፈስ በመነሳሳት ለሀገራዊ መግባባት የበኩሉን አስዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review