የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የሚያደርገውን ግስጋሴ ማጠናከሩን ገለጸ

You are currently viewing የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የሚያደርገውን ግስጋሴ ማጠናከሩን ገለጸ

AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የምክክር ሂደት የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል-አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ገልጸዋል፡፡

ቃል-አቀባዩ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በነበሩት የሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ምክክር ሂደቱ ከመገባቱ በፊት የሚያስፈልጉ የዝግጅት ሥራዎች በሦስት ምዕራፍ ተከፍለው መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ በሂደቱ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር እና የሀገር ውስጥ እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማትን በሂደቱ አጋር ሆነው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ምክክሩን ለማስኬድ የሚያስችል ቁመና ላይ ለመገኘት የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበርም ነው ቃል-አቀባዩ የገለጹት፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሀሳቦችን የማሰባሰብ፣ መመሪያዎችን እና የአሠራር ሥርዓቶችን የመፍጠር እና ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት እንዲሁም ተጨማሪ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበር አንስተዋል፡፡

በዚህም ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ በመሸጋገር የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ የግንዛቤ መፍጠር እና የሀገር ውስጥ እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማትን በሂደቱ አጋር ሆነው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች መከናወናቸውን አመላክተዋል፡፡

በመጨረሻው እና በአራተኛው ምዕራፍም የተሰጠውን ተጨማሪ የአንድ ዓመት ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተሳታፊ ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብን ጨምሮ ያላለቁ ሥራዎችን በመጨረስ ወደ ምክክር ሂደቱ የሚያደርገውን ጉዞ ማጠናከሩን ገልጸዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review