የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ሁለት አዋጆችን አፀደቀ
AMN – ሚያዝያ 09/2017
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ስብሰባው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በ25ኛ መደበኛ ስብሰባው ቅድሚያ የተመለከተው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ነው።
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የመገናኛ ብዙሃንን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1374/2017 አድርጎ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

በመቀጠልም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ አህመድ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በስፋት ከተወያየ በኋላ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን አዋጅ ቁጥር 1375/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።