AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ገቢራዊ በተደረጉ አዳዲስ እሳቤዎች በየዓመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም መገንባቱን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
ሚኒስትሯ ከብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ በሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ልማት ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎችና ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም እያደገ የመጣውን የሥራ ዕድል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የ10 ዓመት ዕቅድ ተነድፎ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል።
በዚህም በየዓመቱ 2 ሚሊዮን የሥራ ዕድል በመፍጠር በዕቅዱ መጨረሻ 20 ሚሊዮን ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን አንስተዋል።
ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ ዕሳቤዎችን መሰረት በማድረግ ዕቅዱ ላይ ክለሳ መደረጉን ጠቁመው ይህም በአገር ደረጃ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅምን ማሳደጉን ተናግረዋል።
የክህሎትና ፈጠራ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት አዳዲስ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸው፤ ይህም በመስኩ ስኬታማ ሥራዎችን ለማከናወን ማስቻሉንም አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ሙፈሪያት ገለጻ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅምን ውጤታማ ለማድረግ ተግባራዊ በተደረጉ የብልጽግና እሳቤዎች በየዓመቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የውጭ አገር ኩባንያዎችን ስራ መሥራት የሚያገኙበት ዕድል መመቻቸቱን የገለጹት ሚኒስትሯ በአጭር ጊዜ ከ80 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመልክተዋል።
የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡና በስነ ልቦና ተዘጋጅተው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በተዘረጋው የድጋፍና ክትትል አሰራር ወደ ውጭ ለስራ የሚሰማራው ዜጋ ቁጥር እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የማጠናከርና የቅበላ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ጎን ለጎን መሰራቱንም አስረድተዋል።
በዚህም ተቋማቱ በአጫጭርና መደበኛ የስልጠና መስኮች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን በየዓመቱ ተቀብለው የማሰልጠን አቅም መፍጠራቸውንም አብራርተዋል።
በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ማየትና መጠቀም እንዲሁም ጠንካራ ተቋማዊ አደራጃጀት መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገው የለውጥ እሳቤ ለተገኙ ስኬቶች መሰረት መጣሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።