የሌባ ተቀባዮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing የሌባ ተቀባዮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

AMN – ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ/ም

ፖሊስ ባከናወነው ተከታታይነት ያለው ጥናት የሞባይል IME ቁጥሮችን የሚቀይሩና የሌባ ተቀባዮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡

ፖሊስ የህብረተሰቡን የመረጃ ሰጪነት አቅም በማጎልበትና በመጠቀም የወንጀል መከላከል ስራዎቹን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ/ም በክ/ከተማው ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ይርጋ ኃይሌ የገበያ ማዕከል አካባቢ ባደረገው ጥናት የሞባይል IME ቁጥሮችን የሚቀይሩና የተሰረቁ የሞባይል ስልኮችን ገዝተው የሚሸጡ ወይም የሌባ ተቀባዮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፖሊስ አስቀድሞ ከህብረተሰቡ የመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ባደረገው ተከታታይነት ያለው የሌባ ጥናትም ተጠርጣሪዎቹ የተሰረቁ የሞባይል ቀፎዎችን ገዝቶ ከመሸጥ ባለፈ IME ቁጥሮችን በመቀየር የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተረጋግጧል፡፡

ተገቢውን የፍርድ ቤት የመበርበሪያና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣትም በተከናወነው ኦፕሬሽን እስካሁን የተለያየ ሞዴል ያላቸው ያላቸው 90 ስማርት ስልኮች፣ 7 ላፕቶፕና 2 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች፣ 14 ታሌቶች፣ 6 ሀርድ ዲስክ፣ 1 ኢንተርኔት ራውተርና የተለያዩ የኤክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከ22 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ውለዋል፡፡

ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራን በማስፋት ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በተለይም የጠፉ ሞባይል ስልኮች ከነጭራሹ እንዳይገኙ የስልኮቹን ባለ 13 ዲጂት መለያ IME ቁጥሮችን በመቀየር የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች ላይም የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ ማስታወቁን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review