የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጸደቀ

You are currently viewing የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጸደቀ

AMN- ጥር 19/2017 ዓ.ም

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረጋቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ የሚውል እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴር ዲኤታ ወ/ሮ መሰረት ሃይሌ፣ ረቂቅ አዋጆቹን በተመለከተ የተዘጋጀውን አጭር መግለጫና ሞሽን ያቀረቡ ሲሆን፤ የብድር ስምምነቶቹ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከርና የመንግስት አገልግሎትን ለማሻሻል ስለመዋላቸው ገልጸዋል፡፡

ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው ብድር በኢትዮጵያ መንግስት በፋይናንስ ዘርፍ ላይ በመወሰድ ያሉትን የሪፎርም እርምጃዎች የሚደግፍና በቀጣዮቹ 5 ዓመታት የሚተገበር የፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ለፋይናንስ ዘርፉ ማጠናከሪያ የተገኘው ብድር 700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሰረታዊ የመዋቅር ማሻሻያ ለማድረግና ካፒታላቸውን ለማሳደግ እንዲሁም ዘርፉን ከአለም አቀፍ የባንክ ስርዓት ደረጃ አንጻር የተጣጣመ እንዲሆን ድጋፍ ስለመስጠቱ ወ/ሮ መሰረት አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረመውና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተገኘው 70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር የመንግስት ፋይናንስን በብቃት ለማሰባሰብና ለማስተዳደር እንዲሁም ውጤታማ ሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር የሚያስችል ተቋማዊ አቅምን ለማጎልበት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

የተደረጉት የብድር ስምምነቶች ከወለድ ነጻና ባንኩ በሚወስነው መሰረት ጥቅም ላይ ባልዋለው ገንዘብ እስከ 0.5 በመቶ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት ስለመቻሉም እና የ6 ዓመት የችሮታ ክፍያን ጨምሮ በ38 ዓመት ጊዜ ተከፍለው እንደሚጠናቀቁም ተጠቁሟል፡፡

የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረገችው የብድር ስምምነት የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነትና ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማሻሻል ያስችላል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል አቅምን እንደሚያሳድግ ገልፀው፤ ብድሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን አሰራር ለማዘመን ያስችላልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የዕዳ ጫናዋ እየቀነሰ መምጣቱንም ነው የተናገሩት።

ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቶቹ ላይ ከተወያየ በኃላ ስምምነቶቹን በ3 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review