መንዙማ ከእስልምና መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ጥሪ ማድረጊያ ነው። የሃይማኖት ተግባራትን መከወኛ ነው። መንፈሳዊ ግጥም በመንፈሳዊ ዜማ የሚታጀብበት ጥበብም ነው፡፡ መንዙማ የኢትዮጵያ መለያና መገለጫ ነው። ግልጽ እና የተጨመቀ መልዕክትም ያስተላልፋል፡፡ እኛም 1446ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ መንዙማ ስላለው ሃይማኖታዊ እና ዓለማዊ ጠቀሜታ ለመዳሰስ ወደድን፡፡
መንዙማ በስልታዊ ግጥሞችና ዜማ የሚቀርብ፣ አብሮነትንና መቻቻልን የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙ አይነት ግጥሞችና ቅርጾች ያሉት ሲሆን ሁሉም ሰው አይጽፈውም፤ የመንዙማ ግጥምና ዜማ ቁርኣንና ሃዲስን ጠንቅቀው በሚያውቁና በተማሩ ሰዎች የሚጻፍ እንጂ፡፡
ወጣት ሰኢድ መሃመድ የምናራ ፕሮዳክሽን መስራችና ባለቤት ነው። በመንዙማና ነሺዳ ስራ ከተሰማራ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው ማብራሪያ እንደገለጸው፣ መንዙማ የአላህን ችሎታና ሊቅነት ለመግለጽ ያገለግላል። የነብዩ መሐመድ ታሪክ የሚገለጽበት መንገድ ነው፡፡ ለእርሳቸው ክብር የሚቀርብበትም ነው፡፡ ለአብነትም ከሙዓዝ ሀቢብ ስራዎች ውስጥ ጥቂት ስንኞችን እንምዘዝ፡-
ያንቱ ፍቅር ያንቱውማ መውደድ
ቤት ቀልሶ ይኖራል ከኔው ሆድ
ችሎ አይገልፀው የኔ ዜማየም መድ
አያስቀምጥ አያስቆም አያስኬድ…
ያላህ ፀጋ ያደለኝ ሽልማቴ
አለኝ ብዬ ምኮራበት ወረቴ
ደስታ ሳቄ አፊያዬ መድሃኒቴ
ሚስጥሬ አንቱ መሸሸጊያ ቤቴ…በማለት ለፈጣሪ ምስጋናና ፍቅርን ይገልጻል፡፡
“መንዙማ በራሱ ማህበራዊ ህይወትን ይዳስሳል፡፡ ከጎረቤትና ማህበረሰቡ ጋር ሊኖር ስለሚገባው ትስስር፣ መረዳዳትና መተጋገዝ ያስተምራል። መቻቻልና አብሮነቱን ያስገነዝባል፡፡ በህይወታችን መስራት ያሉብንንና የሌሉብንን ነገሮች ያስረዳል፡፡ ስለሞት ያስታውሳል። የነብዩ መሐመድ ስብእናና ሥነ ምግባር፣ ማህበራዊ ትስስር በግጥምና በዜማ ተገልጾ ሰዎች በቀላሉ እንዲረዱት ያግዛሉ፡፡ በዚህም መንዙማ ከመቻቻል፣ ከአብሮነት፣ ከሥነ ምግባር አንጻር ከፍተኛ አበርክቶ አለው” ሲልም ወጣት ሰኢድ ያብራራል፡፡ ከዚህ ባለፈም መንዙማ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ለእስልምና ያላትን ክብር ያንጸባርቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም የሰርግ መንዙማዎች አሉ፡፡ የትዳር ምንነት፣ ህይወትን መምራት፣ የትዳር ጥቅሞችን በተመለከተ መልዕክት እና ትምህርት ያስተላልፋል ይላል፤ ወጣት ሰኢድ፡፡ ለአብነትም፡-
…ሙሽሮቹ በጣም ታምራላችሁ መንገዳችሁ ሃላል ይሁን ጎዳና
ደስታቸውን መርቅላቸው በሙሃባ ይኑሩ በደህና
እንደዛሬው እንደተዋባችሁ ፈገግታችሁ ይዝለቅ አማና
ትዳራችሁ በሙሃባ ደምቆ አሸብርቆ ኑሩ በጤና…የሚለውን “ለሙሽሮች ደስታ” የመህፉዝ አብዱ የሰርግ መንዙማ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሌላኛው የመንዙማና ነሺዳ ባለሙያ አብዱልከሪም ጀማል እንደሚለው ደግሞ መንዙማ በባህሪው በጣም ውስን በሆኑ ቃላትና በዜማ ታጅቦ የሚቀርብ ጥበባዊ ስራ ስለሆነ ስለ ዕምነቱ አስተምህሮ በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ነብዩ መሐመድ የከለከሏቸው ድርጊቶችና ምዕመኑ ሊተገብሯቸው የሚገቡ መርሆች አሉ፡፡ እነዚህን እስላማዊ ህጎች በመንዙማ አማካይነት እንዲያውቃቸው ሥራዎቹ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የተከለከሉ እንዲሁም መፈጸም አለባቸው ተብለው በነብዩ የተደነገጉ ህጎች ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆኑ ሥነ ምግባራዊና የመልካም ስብዕና ባለቤት እንድንሆን መንገድ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

ነብዩ መሐመድ ካስተማሯቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የጋብቻ ሥርዓት ክቡርነት ነው፡፡ ታዲያ በመንዙማና ነሺዳ አማካይነት ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ፋይዳ ስላለው “ጋብቻ” ምንነትና አስፈላጊነት ተነግሮበታል፡፡ የሰከነ ህይወት የሚመራበት ስርዓት እንደሆነም አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
መንዙማ ነብዩ መሐመድን በማወደስ ውስጥ ህዝበ-ሙስሊሙን ያስተምራል። የነብዩን ፈለግ በመከተል ሰላምን፣ እርስ በእርስ መተሳሰብን፣ አብሮነትን፣ ወዳጅነትን፣ መረዳዳትንና፣ አንድነትን በመንዙማ አማካይነት ይሰበካል፡፡ ከዚህ አንጻር የመንዙማ ስራዎች ፋይዳቸው ጉልህ መሆኑን በመገንዘብ ይበልጥ መጠበቅና ትውልዱ እንዲያውቃቸው በተለያየ መንገድ ማስተማር ይገባል፡፡
መንዙማን ምን ያህል ተጠቅመንበታል?
መንዙማ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን በሚገባ እና ያለውን አቅም ያህል ተጠቅመንበታል ለማለት አያስደፍርም። በርካታ የመንዙማ ስራዎች ላይ በዳይሬክተርነት የተሳተፈው ሰኢድ መንዙማ በዩኔስኮ መመዝገብ ያለበት ቅርስ ነው፡፡ ይህ መሆን አልቻለም። እድሉንም አልተጠቀምንበትም። መንዙማ ውስጥን የሚቀይሩ፣ ሰው የሆንን ሁሉ የሚያስተምሩ ግጥሞች አሉት፡፡ ትልቅ እና ብዙ ሃሳብን በአጭር ግጥምና ዜማ ማስረዳት የሚቻልበት፣ ታሪክና ቁርዓን ተሳስረው የሚቀርቡበት እውቀት ነው ሲል ያስገነዝባል፡፡
መንዙማ የሚያንጸባርቀው ሃሳብ ትልቅ ነው፡፡ በውስጡም አብሮነትን፣ መተጋገዝን፣ መደጋገፍን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን ይገልጻል። ለአብነትም ከአራት ዓመት በፊት በሙንሺድ ሷሊሕ “ሀገሬ” በሚል የተሰራውን መንዙማ መጥቀስ ይቻላል፡፡
..ኧ…መገን፣ መገን፣ መገን
የሰው ልጅ ወገን፤ የሰው ልጅ ዘመድ
የነጃሺ ልጅ፤ የሰይድ ቢላል
የታሪክ ዓምዱ መች ዘመም…፡፡
ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሃሳቡን ያጋራው ሌላኛው የነሺዳ እና የመንዙማ ባለሙያ ወጣት መሀመድ ሙሰማ፤ “መንዙማ ፈጣሪን ከማመስገን እና ከማወደስ፤ ለፈጣሪ እና ለነብዩ መሐመድ ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት ከመግለጽ፤ ለነብዩ መሐመድ የሚቀርብን ውዳሴ እና አስተምህሮቶቻቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ለህብረተሰቡ ከማድረስ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ መንዙማ ሀገርኛ ይዘት ያለው ድቤን የሚጨምር እና በርካቶችን ሊያሳትፍ የሚችል ነው። ለዛ ያላቸው ይህ መወደስ የማንኛውም ሰው ቀልብ እንደሚስብ እና በውስጡ የሚተላለፈውን መልዕክት በአንክሮ እንዲከታተሉ የማስገደድ አቅም እንዳለውና በትኩረት ሊሰራበት ይገባል” ሲል አስረድቷል፡፡
ወጣት ሰኢድ እንደሚለው፣ በሀገራችን ገና ያልተሰሩና ያልወጡ በርካታ የመንዙማ ግጥሞች አሉ፡፡ እነዚህ መውጣት አለባቸው፡፡ መንዙማ ገና ያልተነካ ዘርፍ ነው፡፡ ከዲጂታል ዓለም በፊት ለመቶ ዓመታት የተሰሩ ስራዎች በራሱ አስገራሚና በጥልቀት መመርመር ያለባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደ ሀገር እነዚህን ሃብቶች አውጥቶ መጠቀም ያስፈልጋል ፡፡
መንዙማ በዲጂታሉ ዓለም
መራመድ ያለብን በጊዜው መንገድ ነው፡፡ በአንድ ዘመን ኦዲዮ መንዙማን ተደራሽ ለማድረግ ተመራጩ መንገድ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰው ቪዲዮ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፕሮዳክሽን ጥራትን ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
ሰኢድ “ካሴት በነበረበት ጊዜ በካሴት ሰርተናል፡፡ ሲዲ በነበረበት ጊዜ መንዙማ በሲዲ ይቀርብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ዲጂታል ሚዲያ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ይህ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ከሀገር ውጭ ተጽእኖ ለመፍጠርና ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ዲጂታሉ ዓለም ድንበር አይገድበውም፡፡ ስለዚህ ከዘመኑ ጋር አብሮ መራመድና መንዙማን በዲጂታሉ ዓለም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል” ብሏል፡፡
መንዙማ ዲጂታል ላይ ገና በበቂ ሁኔታ አልተሰራበትም፡፡ ከዚህ በላይ መሰራት አለበት፡፡ በተለያየ ቋንቋ መሰራት አለበት፡፡ መተርጎም አለበት። በተለያዩ ሀገራት በመሄድ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ሲልም አክሏል፡፡
መንዙማን ለማስተዋወቅ ምን ይሰራ?
“እኔ እንደ ግለሰብ መንዙማ ላይ ማድረግ የምችለው አስተዋጽኦ አለኝ” የሚለው ሰኢድ፣ ሁሉም በማስተዋወቅ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አብራርቷል፡፡
“መንዙማ ስሰራ ‘ግጥሙ ምን መሆን አለበት፣ ቪዲዮዎቹ ምን ማስተላለፍ አለባቸው’ በሚለው ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥቼ እሰራለሁ፡፡ ሌላውን ወደፊት ተራመድ ለማለት እኔ አንድ እርምጃ መራመድ አለብኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ ከሌላ ሀገር ዩኒቨርሲቲ ጋርም በዘርፉ ቢሰሩ መልካም ነው፡፡
በተጨማሪም የእምነት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን መንዙማን ከማስተዋወቅ አንጻር ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በስራው ላይ የተሳተፉ ወጣቶችን በማበረታታትና በዓለም ላይ በደንብ በማስተዋወቅ እንደ ሀገር ለቱሪዝም ገቢ ትልቅ አቅም መፍጠር ይቻላል። መንዙማ ከሃይማኖት አልፎ እንደ ሀገር ተጠቃሚ የሚያደርገን ሃብት ነው፡፡ ሁሉም ባለው አቅም የበኩሉን አስተዋጽኦ ቢያደርግ መንዙማን ከዚህ በላይ ማሳደግ ይቻላል” ሲል በማጠቃለያ ሃሳቡ አንስቷል፡፡
በጊዜው አማረ