ባለፉት ቀናት በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የቴአትር መርሃ ግብር፣ የስዕል አውደ ርዕይ፣ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶች እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
‘የትዝታዬ ማህደር ግለታሪክ’ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ ደራሲ ጌታቸው በለጠ የራሱን ህይወትና ስራዎች ያካተተበት ይህ ግለ ታሪክ መጽሐፍ፣ በከፍተኛ የህትመት ጥራት በ448 ገጽ የተዘጋጀ ነው፡፡ ደራሲ ጌታቸው በማህበራዊ የትስስር ገጹ ስለመጽሐፉ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ “በግል እምነቴ መጽሐፉ ግለ ታሪክ ይባል እንጂ የሀገር ታሪክ ጭምር መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ” ብሏል። መጽሐፉን በቀጥታ ከደራሲው እጅ ለመግዛት የሚፈልጉ አንባብያን “ፊርማዬን አኑሬ በሚገኙበት አድራሻ ወይንም አመቺ ቦታ እንዲደርሳቸው አደርጋለሁ” ብሏል።
ሥዕል
ግዙፉ አውደ ርዕይ ለሃያኛ ጊዜ ሊካሄድ ነው፡፡ በጥበብ አፍቃሪያኑና በጥበበኛው ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ’The Big Art Sale’ ዓውደ ርዕይ በዚህ ዓመት ለሃያኛ ጊዜ በሒልተን ሆቴል የፊታችን ሚያዝያ 4 እና 5 2017 ዓ.ም ይካሄዳል። ኢቨንት አዲስ ሚዲያ እንደዘገበው፣ በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለጎብኚዎችና ለገዢዎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ ከጥበብ ስራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ሲኖሩ፤ ለልጆች ልዩ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ ይህ ልዩ ዓውደ ርዕይ ሰዓሊያን ሥራቸውን እንዲሸጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ገቢውም ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል ተጠቁሟል።
በሌላ መረጃ፣ የሰዓሊ ሄኖክ ፀጋዬ “በመንገዴ ላይ” የሥዕል ዓውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ረዕቡ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ቦሌ በሚገኘው እንጦጦ ጋለሪ በይፋ የተከፈተው ይህ አውደ ርዕይ፣ ሰዓሊው ተፈጥሮ እና ታሪክን መነሻ በማድረግ የሰራቸው የጥበብ አሻራዎችን ለዕይታ ያበቃበት ነው ተብሏል፡፡ ሰዓሊው የሥነ ጥበብ አፍቃሪያንም መጥተው አውደ ርዕዩን እንዲመለከቱ ጋብዟል፡፡ ይህ አውደ ርዕይ እስከ መጪው ሚያዝያ 7 ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

ኪነ ጥበባዊ የውይይት መርሃ-ግብር
ለአንጋፋው አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ የምሥጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር ይካሄዳል፡፡ ተስፋ የኪነ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ እና የኪሮስ ኃይለሥላሴ ልጆች በጋራ ያዘጋጁት ይህ መሰናዶ ዛሬ ቅዳሜ ከቀኑ 9:30 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ይደረጋል፡፡
በመርሃ ግብሩ በዕለቱ፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር እንዲሁም መሐሪ ብራዘርስ ባንድ ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር በመሆን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በስሙ የተዘጋጀና በታዋቂ ተዋንያን የሚቀርብ አጭር ድራማ፣ ሕይወቱንና ስራዎቹን የሚዘክር ዶክዩመንተሪ ፊልም እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ይቀርባሉ።
አርቲስት ኪሮስ፣ “ሳልሳዊው ባልንጀራ”፣ “የቬኑሱ ነጋዴ” ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ”፣ “ጣውንቶቹ “፣ “አሉ “፣ “ባልቻ አባነፍሶ”ን የመሳሰሉ ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። በርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተውኗል። ሀገር ፍቅር ቴአትር እና የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮን በተለያዩ ጥበባዊ ኃላፊነቶች ሰርቷል። በሚሊኒየሙ ጊዜ የአዲስ አበባ ሚሊኒየም ጽህፈት ቤትን በሊቀመንበርነት መርቷል።
በሌላ መረጃ 88ኛው የስብሐቲዝም መድረክ ነገ ይደረጋል፡፡ “በገናን ከዝማሬ መሣሪያነቱ ባሻገር እንዴት ባለ አረዳድ እንረዳው?” በሚል መነሻነት የሚካሄደው ይህ መሰናዶ፣ የበገና መምህሩ ተፈራ ጥላሁን የመወያያ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡ መርሃ ግብሩ ነገ እሁድ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ይደረጋል፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ በዚሁ ቴአትር ቤት በ8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን፤ 11፡30 ሰዓት ላይ ደግሞ እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር፣ “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ