የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

ባለፉት ቀናት በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የአዳዲስ መጽሐፍ ህትመት፣ የመጽሐፍ አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጻሕፍት

ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አውደ ርዕይ በይፋ ተከፍቷል። ስድስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ውስጥ የተጀመረው የመጽሐፍ አውደ ርዕይ አዳዲስ ለህትመት የበቁትን ጨምሮ የተለያዩ መጻሕፍት ለሽያጭ አቅርቧል፡፡ 17ኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የመጽሐፍ አውደ ርዕይ እስከ ግንቦት 4 ቀን ድረስ ይቆያል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ አዳዲስ መጻሕፍት ይመረቃሉ፣ ዳግም የታተሙ መጻሕፍት ለሽያጭ ይቀርባሉ ተብሏል።

“ለጋስ አድማስ” መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ በገጣሚ ወልደገብርኤል ደሳለኝ(ወገደ) የተዘጋጀው “ለጋስ አድማስ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ ለአንባቢያን እንደሚደርስ ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ “ለጋስ አድማስ” የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ሲሆን በ350 ብር በቅደመ ሽያጭ ለአንባቢያን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ሥነ-ጥበብ

የስዕል ውድድርና ኤግዚቢሽን በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ተከፈተ፡፡ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ጋር በመተባበር “ሀገራዊ ድምቀት በጥበባት ህብረት” በሚል መሪ ቃል የኪነ ጥበቡ ማህበረሰብና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የሥዕል ውድድርና ኤግዚቢሽን በይፋ ተከፍቷል።

የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞረዳ ኤግዚቢሽኑን መርቀው በከፈቱበት መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት “ስዕሎችን የምንስለው ተፈጥሮን መሰረት በማድረግ ነው” ብለዋል፡፡ “ለሁሉም ሰዓሊያን ምቹ የሆነ አዕምሮን የሚያድስ ማራኪ ቦታ በሆነው በጉለሌ እፅዋት ማዕከል ለእንደዚህ አይነት ጥበባዊ ስራዎች ምቹ ቦታ በመሆኑ ሁሉም የጥበቡ ማህበረሰብ እንዲጠቀምበት የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራ” ጥሪ አስተላልፈዋል።

የቢሮው የኪነ ጥበብ ሀብቶች ልማት መድረኮች እና ኩነቶች ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደኑ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ቢሮው ኪነ ጥበብን ከማስፋፋትና ከማሳደግ አኳያ በተለይም አማተር ባለሙያዎችን በማበረታታት፣ በመደገፍና ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ በማመቻቸት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። በከተማችን የሚገኙ የኪነ ጥበብ ስራዎችን በመምራትና በማስተባበር ሰላምን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትንና ሀገራዊ ጉዳዮችን  አጉልተው የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎችን በመከየን በኪነ ጥበብ ስራዎች እያዝናኑ መልዕክት የማስተላለፍ ስራዎች እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡ በይፋ የተከፈተው የስዕል ውድድርና ኤግዚቢሽንም እንደ አንድ ማሳያ የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የስዕል ኤግዚቢሽንና ውድድሩ ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን፤ ዛሬ እና ነገም ዓውደ ርዕዩ ለጥበብ አፍቃሪያን ክፍት ይሆናል፡፡ እንዲሁም በክፍለ ከተማ ደረጃ፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በሥዕል ማሰልጠኛ ተቋማት፣ በህፃናትና በስቱዲዮ ደረጃ ውድድር እንደሚካሄድ ኤግዚቢሽኑን ካስተባበሩ አካላት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ መረጃ “ሕልም እልም” የተሰኘው የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በሰዓሊ ሥዩም አያሌው የተሰሩ ስዕሎች የቀረቡበት ይህ አውደ ርዕይ ሀያት በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ በመታየት ላይ ነው፡፡ ዓውደ ርዕዩ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን የተከፈተው እስከ ፊታችን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የአይዳ ሙሉነህ የፎቶ ግራፍ ዓውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በአይዳ ሙሉነህ ተዘጋጅቶ በ ዘ-ኢንድ ፈንድ አዘጋጅነት እና በሪቺንግ ዘ-ላስት ማይል ድጋፍ ለህዝብ የቀረበው ሪፍሬሚንግ ኔግሌክት የተሰኘ የፎቶ ዓውደ ርዕይ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተከፍቶ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

በገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ማዕከል እየታየ ባለው በዚህ ዓውደ-ርዕይ፣ አይዳ ሙሉነህን ጨምሮ የሰባት አፍሪካዊ የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች ስራ ስብስብ ቀርቦ በመታየት ላይ እንደሆነም ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡

በስራዎቻቸው ጠንካራ ታሪክን በፎቶ የማስቀረት እና ማህበረሰቡ የሚያልፍበትን እውነታ የማንፀባረቅ ድንቅ ችሎታ ያላቸው የስድስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች 54 የሥነ ጥበብ ስራዎችና ዘጋቢ-ፎቶዎች የተካተተበት ዓውደ ርዕይ ሥነ-ጥበብ ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮችን የማጉላት ትልቅ አቅም እንዳለው ያሳያል ተብሏል፡፡ ዓውደ ርዕዩ ባለፈው ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተ ሲሆን፤ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ በብሔራዊ ቴአትር ባሎች እና ሚስቶች ቅዳሜ 8:00 ሰዓት የሚታይ ሲሆን 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴያትር ይታያል፡፡ እሁድ ዕለት ደግሞ በ 8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ደግሞ እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር በብሔራዊ ቴያትር ቤት ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር፣ “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት ደግሞ በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review