የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች

You are currently viewing የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች

ባለፉት ቀናት በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የስዕል አውደ ርዕይ፣ የአዳዲስ መጽሐፍ ህትመት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶች እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

“ደሸቆ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በደራሲ እመቤት ተሾመ ከበደ የተጻፈውና “ደሸቆ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው  አዲስ መጽሐፍ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በ310 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡

“ደሸቆ” የካፊኛ ቃል ሲሆን የጭድ ጥጃ እንደማለት እንደሆነም ተገልጿል። ደራሲ እመቤት ተሾመ ከዚህ ቀደም “ምንሽሮ” በግሏ ከሌሎች ደራሲያን ጋር ደግሞ “የነፍስ እኩያሞች” የተሰኙ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅታለች።

በሌላ መረጃ የዕውቁ ሙዚቀኛ የይሁኔ በላይን ግለ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል ተብሏል፡፡ በራሱ በይሁኔ በላይ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ያለፈበትን የህይወት መንገድ፣ የሙዚቃ ህይወቱና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነው ተብሏል፡፡

የስዕል አውደ ርዕይ

“ህልም አልም” የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ ከነገበስትያ ለእይታ ይበቃል፡፡ የስዕል አውደ ርዕይው ለእይታ የሚበቃው በሀያት እሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ነው፡፡ ሰዓሊው ስዩም አያሌው ሲሆን አውደ ርዕይው እስከ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በእይታ ላይ ይቆያል፡፡

ሙዚቃ

ሦስት ትዉልዶችን በአንድ መድረክ ያጣመረዉ “ሽርጉድ ኮንሰርት” በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ ሦስት ትውልድ በአንድ መድረክ  ያገናኘ ነው የተባለለት የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ  አለማየሁ ሒርጶና ጎሳዬ ተስፋዬ ከ20 ዓመት በኋላ የሚጣመሩበት  “ሽርጉድ ኮንሰርት” ዛሬ ቅድሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓም በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።

የኮንሰርቱ አዘጋጅ “ሽርጉድ ኢንተርቴይመንት” ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ በራማዳ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው በኮንሰርቱ ላይ ከ10 እስከ 13 ሺህ ሰው ይጠበቃል። ኤፍሬም ታምሩ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አለማየሁ ሒርጶና ሜላት ቀለመወርቅ ነግሰው በሚያመሹበት በዚህ መድረክ ያልተጠበቀ ሰርፕራይዝ አርቲስትን ጨምሮ በርካታ ትዕይንቶች ይታዩበታል ተብሏል፡፡ በዚሁ የሙዚቃ ድግስ ላይ የአርቲስቶቹ አድናቂ ትልልቅ እንግዶችም ይገኛሉ፡፡ የኮንሰርቱን የሰዓት ጉዳይ በተመለከተ ሚሊኒየም አዳራሽ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ክፍት የሚደረግ ሲሆን ልክ  3:00 ላይ  ኮንሰርቱ ይጀምራል፡፡ አጃቢ ባንዶቹ በድምፃዊያኑ የተመረጡና በስራቸው አንቱታን ያተረፉ ናቸውም ተብሏል።

በሌላ መረጃ ከ19 ዓመታት የስደት ሕይወት በኋላ ወደሐገሩ የተመለሰው ተወዳጁ ድምፃዊ አለማየሁ ሒርጶ ስለኢትዮጵያ እናቶች ያቀነቀነው አዲስ የሙዚቃ ቪዲዮ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ዕለት ተለቋል። ሙዚቃው የኢትዮጵያ እናቶችን ውለታ የሚዘክርና ለሀገር የዋሉትን ተግባር የሚያስታውስ ነው ተብሏል፡፡

ልዑል ሲሳይ ተከታታይ ኮንሰርት ሊያቀርብ ነው፡፡ የድምፃዊ ልዑል ሲሳይ ኮንሰርት ዛሬ ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት 6 ሰዓት  ድረስ በጊዮን ሆቴል ይካሄዳል። በአዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል የተዘጋጀው ይህ ኮንሰርት እንደተጠናቀቀ ግንቦት 2 በሀዋሳ፣ ግንቦት 23 በድሬዳዋ ሌሎች ድምፃዊያንን በማካተት የኮንሰርት ቱር እንደሚካሄድ ተገልጿል። ከልዑል ሲሳይ በተጨማሪ ስካት ናቲ፣ ሃና ግርማ እና ዊሃ በዝግጅቱ ላይ በቶራ ባንድ ታጅበው ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በዘመናዊ ሙዚቃ በመጀመሪያ አልበም ከፍተኛ ተወዳጅነት እና ተቀባይነት ያገኘው ልዑል ሲሳይ በፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ እና ሸጋ ኤቬንትስ እና ፕሮሞሽን አዘጋጅነት ሀገር አቀፍ የሙዚቃ ቱር “የልዑል ሙዚቃ ቱር” በሚል ስያሜ ያከናውናል። ድምፃዊ ልዑል ሲሳይ “ልዑል” ሲል በሰየመው የመጀመሪያ አልበሙ ውስጥ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ስልተ-ምቶችን ጨምሮ ሬጌና ፖፕ ስልቶችን አካቶ መምጣቱ ይታወሳል።

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች ቅዳሜ 8:00 እና 11፡30 ደግሞ ባቡሩ የተሰኙት ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡ እሁድ በ 8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን፤  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በብሄራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 የሕይወት ታሪክ የሚታዩ ሲሆን፤ “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review