የመዲናዋ ነዋሪዎች የወቅቱን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄዎችን ለያደርጉ ይገባል- ኮሚሽኑ

You are currently viewing የመዲናዋ ነዋሪዎች የወቅቱን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄዎችን ለያደርጉ ይገባል- ኮሚሽኑ

AMN- የካቲት 23/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በሙሉ አቅሙ እያከናወነ ቢሆንም ስራው ለኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ብቻ የሚተዉ ባለመሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችም የወቅቱን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የእሳት አደጋ መደጋገሙን ተከትሎ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደገለጹት፣ ህብረተሰቡ በተለያዩ አማራጮች እየተላለፉ ያሉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ህይወትና ንብረቱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

ለእሳት አደጋ መከሰት እና መባባስ ነፋሻማና ፀሀያማ የአየር ንብረት ምክንያት መሆኑን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ እሳት ከተነሳ በኋላ የሚፈጠር ወይም የተፈጠረ ንፋስ የኦክስጂን አቅርቦትን በመጨመር ቃጠሎ እንዲባባስ እንደሚያደርግ አስገንዝቧል፡፡

ነፋስ ከፍተኛ ሙቀትን በመሸከም እና ፍም በመያዝ በአቅራቢያው ላሉ እና ቀድመው ያልተቀጣጠሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን በተጨማሪ ወደ እሳትነት የመቀየር ሰፊ እድል እንዳለውም አመላክቷል፡፡

ይህም ማለት ንፋስ ከእሳት ጋር ሲገናኝ የኦክስጅን መጠኑንን ስለሚጨምረው እሳቱ እያደገ እንደሚሄድ አስረድቷል፡፡

የንፋስ መኖር በማንኛውም ሰዓት እሳት አደጋ ከማስከተሉም በላይ የመቀጣጠል ሂደትን ከማፋጠን በተጨማሪም የእሳትን አቅጣጫ ሊያስቀይርና የደረሰው አደጋ ከቁጥጥር ውጭ ሊያደርግ እንደሚችልም ነው የገለጸው፡፡

የእሳት አደጋ ተከላካዮች ላይም ስራቸውን በማክበድ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስም አመልክቷል፡፡

ብዙውን ጊዜ በአነስተኛ ብልጭታ በነፋስ የሚነድ እሳት ደን በተከማቸበት ወይም ቁጥቋጦ ባለበት አካባቢ እንደሚፈጠርም አክሏል፡፡

በከተማ አካባቢ በእንጨትና ቆርቆሮ የተሰሩ እንዲሁም ያረጁ መኖሪያ ቤቶች ከመኖራቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ቦታዎች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ አደጋውን ለመቆጣጠር ምቹ መንገድ ባለመኖሩ ነፋሻማ እና ፀሀያማ አየር ንብረት ተጨምሮበት ከፍተኛ እሳት አደጋ እየተፈጠረ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብሏል፡፡

በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች የወቅቱን የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ እና በተለያዩ አማራጮች እየተላለፉ ያሉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በመተግበር ህይወት እና ንብረታቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review