የመዲናዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲፈተሽ

You are currently viewing የመዲናዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲፈተሽ
  • Post category:ልማት

  • የኮሪደር ልማቱ ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱ መልካም እድልን ይዞ እንደመጣ ተገልጿል

የኤሌክትሪክ ጉዳይ ከዕለት ተዕለት ህይወታችን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። በተለይ ደግሞ  የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ መቀመጫ ለሆነችው አዲስ አበባ ደግሞ ዋጋው ከዚህም በላይ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ቀደም ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ቀላል የማይባሉ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር፡፡ እኛም ተቋሙ ይህን ይነሱበትን የነበሩ ችግሮች በመቅረፍ፣ አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ብሎም በማዘመን ረገድ ምን እየሰራ ነው ስንል ልንቃኘው ወደድን፡፡

ጠዋት ለስራ ወጥተው ማታ እንደሚመለሱና ኤሌክትሪክ የሚጠቀሙት በአብዛኛው ማታ ላይ እንደሆነ አስተያየታቸውን ለዝግጅት ክፍሉ የሰጡት የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታፈሰች እርገጤ፣ “የአሁኑ አገልግሎት ከቀድሞው አንፃር ሲታይ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በፊት መብራት ሲጠፋ ቶሎ አይመጣም፡፡ አንዳንዴ ከ3 እስከ 4 ቀን ባስ ሲል ሳምንትም ድረስ ይቆይ ነበር፡፡ አሁን ግን አልፎ አልፎ ቢጠፋም ለሰዓታት ብቻ ቆይቶ ይመጣል። በዚህ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ የትናየት ቦጋለ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ተከራይተው ነው የሚኖሩት። ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አንጻር የሰጡት አስተያየት የወይዘሮ ታፈሰች ንግግር የሚያጠናክር ነው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ መብራት ሲጠፋ ብዙ አይቆይም። ነገር ግን በበዓል ወቅት የመጥፋትና የመቆራረጥ ሁኔታ አሁንም ይስተዋላል፡፡ ለበዓል ቀድመን መዘጋጀት ሲገባን ሁሉንም ነገር በአንድ ላይ ስንሰራ የመብራት ሀይል ማነስና መቆራረጥ ይከሰታል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን አሁን ያለው አገልግሎት መልካም ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ እሸቱ ገድለም ሌላኛው ናቸው፡፡ “ስቶቭ፣ የእንጀራ ምጣድ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን በኤሌክትሪክ ነው የምንጠቀመው። የመብራት ሀይሉ ከበፊቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን  ብዙ ጊዜ የመብራት መስመር ይበላሻል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቢሰራ” ሲሉ ሃሳብ አንስተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጡ ቀድሞ ከነበረው መሻሻል እንዳለው፣ በተለይ መብራት ሲጠፋ ቶሎ እንደሚመጣና የመቆራረጥ ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደተቀረፈ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ሁሉንም በጋራ ድምጽ ያነሱት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጡ ምን ይመስላል? የታሪፍ ማስተካከያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ምን አወንታዊ አስተዋጽኦ አደረገ? የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኑኬሽን ስራ አስፈፃሚ የሆኑትን አቶ መላኩ ታዬን አነጋግረናል፡፡

እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፣ በሀገራችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቀድሞ ለብርሃን ብቻ ነበር የምንጠቀምበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከኤሌክትሪክ ጋር ብዙ ቁርኝት አለን፡፡ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን ለሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት እየሆነ መጥቷል፡፡ ከምግብ ማብሰል ጀምሮ ለትራንስፖርት አገልግሎት ለአብነት ቀላል ባቡር፣ የኤሌክትሪክ መኪና፣ ትምህርት በኤሌክትሪክ አማካኝነት በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የጤናው ዘርፍና ሌሎች ዘርፎች ኤሌክትሪክን በመጠቀም የሚሰጡ በመሆናቸው ኤሌክትሪክ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጀርባ ያለና የመሰረተ ልማቶች አውራ ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማስተካከያን በተመለከተ አቶ መላኩ ሲያብራሩ፣ በዘንድሮው ዓመት ማስተካከያ ሲደረግ መንግስትም ድጎማ አድርጓል፡፡ ይህም እስከ 50 ኪሎ ዋት ሰዓት በወር የሚጠቀሙ 75 በመቶ፣ እስከ 100 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቀሙ 40 በመቶ፣ እስከ 200 ኪሎ ዋት ሰዓት የሚጠቀሙ 4 በመቶ ይደጎማሉ፡፡ ከ500 ኪሎ ዋት ሰዓት በላይ የሚጠቀሙ የታሪፍ ማሻሻያውን ያለምንም ድጎማ እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አብዛኛው ህብረተሰብ ከ50 ኪሎ ዋት ሰዓት በታች የሚጠቀም ነው፡፡ የታሪፍ ማስተካከያው የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበና ድጎማ የተደረገበት በመሆኑ ከፍተኛ ጭማሪ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ መሻሻል የታየበት ቢሆንም አሁንም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር እንዳለ ነዋሪዎች ላነሱት ጥያቄ አቶ መላኩ በሰጡት ምላሽ፤ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ከዛፍ ጋር ተቀራርበው የተተከሉ መሆኑ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት፣ ረዥም ዓመታት ያገለገለ መሰረተ ልማት መሆኑና ዘመናዊ አለመሆኑ፣ የብልሹ አሰራር መኖር ለሀይል መቆራረጥ ዋነኛ ምክንያት ናቸው፡፡ በዚህም ነዋሪዎች እንዳነሱት ቀድሞ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ በየጊዜው ያጋጥም፤ ረዥም ሰዓትና ቀናትም ይቆይ ነበር። የተቋረጠበትን አካባቢ ለማወቅም ደንበኞች በስልክ ወይም በአካል ካልነገሩን ማወቅ የምንችልበት ቴክኖሎጂ አልነበረም።

በአሁኑ ወቅት ግን አዲስ አበባን ጨምሮ በዙሪያዋ 50 ኪሎ ሜትር ሬድዬስ ድረስ የኔትዎርክ ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሰራ ተሰርቷል፡፡ ሌላው በሲስተም መረጃን ወደ ማዕከል የሚልክ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሀይል የተቋረጠበትን ምክንያት በማወቅ የጥገና ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡

አቶ መላኩ እንዳስረዱት፤ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ለሃይል መቆራረጥ 47 በመቶ የሚሆነው ምክንያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዛፎች በቅርበት መኖራቸው ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ዛፍም ሆነ ግንባታዎች ከኤሌክትሪክ መስመር በሦስት ሜትር ሬድየስ መራቅ አለባቸው፡፡ በዚህም ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቱ በሦስት ሜትር ቅርበት ያላቸውን ዛፎች የመቁረጥ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ይህም ህብረተሰቡ ግቢው ውስጥ ዛፍ ይተክላል፡፡ የኤሌክትሪክ ምሰሶ አጠገብ በመሆኑ የሀይል መቆራረጥ እንዳያስከትል እንዲቆረጥ ሲጠየቅ ፈቃደኛ የማይሆን እያጋጠመ በመሆኑ በጋራ ሆነው ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ደግሞ ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መልካም እድልን ይዞ እንደመጣ የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ ልማቱ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መስመሮች መሬት ስር ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲዘረጉ አስችሏል፡፡ ይህም ለመብራት መቆራረጥ ችግር አንዱ መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በሲም ካርድ የሚሰራ ዘመናዊ ቆጣሪ ስማርት ሜትር የተተከለ በመሆኑ በዚህ ቴክኖሎጂ መረጃውን በማየት የመብራት መቆራረጥ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን በማዘመን በተሰራው ስራ ሃይል የመቆራረጥ ችግር ሲያጋጥም ወዲያው መረጃውን ማወቅ እና የሃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ እና ከተቋረጠ በኋላ የቆይታ ጊዜውን ማሳጠር ተችሏል፡፡ በቀጣይም የበለጠ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ በየጊዜው የአሰራር ስርዓት ማሻሻያ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በአገልግሎቱ ላይ ውጤት መታየቱንም አቶ መላኩ ያስረዳሉ፡፡ ለአብነት፡- ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ለመክፈል ነዋሪው ረዣዥም ሰልፍ በመሰለፍ ይጉላላ ነበር፡፡ በዚህም ለምሬት ተዳርጎ ነበር፡፡ ይህ ተቀይሮ ከ90 በመቶ በላይ ደንበኞች በዲጂታል የክፍያ አማራጮች በመጠቀም ባሉበት ቦታ በሲቢኢ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በቴሌ ብር፣ በአዋሽ ፕሮ ክፍያ በመፈፀም አገልግሎቱን እያገኙ ነው፡፡ ይህ አሰራር የተገልጋይን እንግልት ያስቀረና ተቋሙም ገቢውን በወቅቱ በማግኘት መልሶ ስራ ላይ ለማዋል ሰፊ እድል የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፣ ከብልሹ አሰራርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሙያውና አመራሩ የቅንነት መንፈስ ተላብሰው እንዲያገለግሉ በተለያዩ ጊዜያት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ ነው። ከዚህ አልፎ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቀ አካል ካለ ከአስተዳደራዊ እርምጃ እስከ ስራ ማሰናበትና ወደ ህግ የማቅረብ የደረሰ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ አኳያ በተያዘው በጀት አመት ከሀምሌ እስከ ህዳር 30 ባሉት አምስት ወራት ለአብነት፤ አዲስ ተገልጋዮችን በህገ ወጥ መንገድ ያለአግባብ ያስተናገዱ፣ ተቋሙ ለሚያስከፍለው አገልግሎት ሂሳብ ቀንሶ በማስከፈል ተቋሙ እንዲጎዳ ያደረጉ፣ ትራንስፎርመር ከአቅም በላይ በመጫን እንዲቃጠል ያደረጉ 20 ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ደመወዝ መቆረጥ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ማንኛውም አካል በአገልግሎቱ ላይ ቅሬታ ካለው በአካል መምጣት ሳይጠበቅበት በእጅ ስልኩ ሞባይል በመጠቀም ብቻ ጥቆማ፣ ቅሬታና አስተያየት ማቅረብ የሚችልበት አሰራር ለመዘርጋትና አገልግሎቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቀጣይም የደንበኛ እርካታን በማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን በማዘመን፣ ተቋማዊ አቅም ግንባታ በማካሄድ ዘመናዊና ጥራት ያለው አሰተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑንም የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚው አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review