የመዲናዋ የውበት ሰበዞች
በአብርሃም ገብሬ

ዘመናዊነት ካመጣቸው እሴቶች መካከል አንዱ ከተሜነት ነው፡፡ ከተሞች ደግሞ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚያዊ ዕድገት፤ የማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ማዕከል ናቸው፡፡ በጽንሰ-ሃሳብ ደረጃ ከተሞች ውስጥ ሰዉ አብዛኛው ስራውና ገቢው ከግብርና ውጪ የሆነ፤ የተሻለ መሰረተ ልማት ያሉት፤ የመኖሪያና መስሪያ ቦታው ዘመናዊ አኗኗር የሚታይባቸው ስፍራዎች ናቸው፡፡ ከተሞች ከጥንት ጀምሮ የአስተዳደር፣ የባህል፣ የአገልግሎት ማዕከሎች እና የዕድገት ምሰሶዎች በመሆንም ይታወቃሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ከተሞችን በሥርዓት መምራትና የነገውን ትውልድ ጭምር ታሳቢ አድርጎ በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ማሻሻያዎችን ማድረግ እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ ይሁንና መዲናችን አዲስ አበባ በውስጧ ብዙ ዕሴቶችን ይዛ የኖረች ከተማ ብትሆንም በዚያው ልክ ደግሞ በርካታ ጉድለቶችም ይዛ የኖረች ከተማ ነች፡፡
አሁን ላይ በለውጥ ሂደት ላይ ያለችው አዲስ አበባ፣ ከዚህ ቀደም ጎዳናዎቿ ደርዝ አልነበራቸውም፡፡ የአይን ማረፊያ የሚሆኑ ስፍራዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ፈልጎ ማግኘት ብርቅ ነበር፡፡ ‘እስኪ በእግሬ ልንሸራሸር’ ብሎ በአጋጣሚ ከቤቱ ለወጣ ሰው ብዙም የሚመቹ አልነበሩም፡፡ እነዚህንና ሌሎች የአዲስ አበባን እንከኖች መዲናዋ የዕድሜዋን ያህል አለመዘመኗና ዕድገት አለማሳየቷ መገለጫ አድርገን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡
ይሁንና አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልከ-ብዙ ውብ ገጽታዎችን እየተላበሰች ነው፡፡ ጎዳናዎቿ ሰፍተው፤ በውብ መብራቶች ተሽቆጥቁጠው፤ አረንጓዴ ለብሰውና በፋውንቴኖች ውበት ታጅበው እየፈኩ ናቸው፡፡ ይህ የመዘመን ጉዞ ደግሞ አሁን ላይ አዲስ አበባን ልትጎበኝና ለመዝናናት የምትመረጥ ከተማ እያደረጋት ይገኛል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አካባቢ የተሰሩ ፋውንቴኖችና በአበባ ያጌጡ ስፍራዎች ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጭና ለከተማዋ ዕድገትና ገጽታ ያላቸውን ሚና በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡
የከተማዋ አዳዲስ የመዝናኛ አማራጮች
የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባን የውበት ማሳያ እየሆኑ ያሉ አዳዲስ ፋውንቴኖችና በአበባ ያጌጡ ማረፊያ ቦታዎችን ዞር ዞር በማለት ቃኝቷል፡፡ በዚህ ቅኝት ወቅትም በመዲናዋ እየተሰሩ ያሉ ፋውንቴኖች በአዲስ አበቤዎች በመዝናኛ አማራጭነት እየተመረጡ እንዳለ ለመመልከት ችሏል፡፡ በዚህ መሰረት ከቀበና አንስቶ እስከ ፒያሳ ባደረግነው ቅኝት በየቦታው ምቹ ማረፊያ ስፍራዎችና ፋውንቴኖች ለነዋሪዎች አዳዲስ የመዝናኛ አማራጮች እየሆኑ ናቸው፡፡
አራት ኪሎ የአዲስ አበባ ህፃናትና ወጣቶች ትያትር ቤት የውጭ በር አጠገብ ተለቅ ያለ ግራር አለ፡፡ ቅርንጫፎቹ ጥላ ሆነው ሰውን ያሳርፋሉ። በግራሩ ዙርያ የተሰሩ ምቹ ማረፊያ ወንበሮች፣ ፋውንቴንና አበባዎች በእግር እየተጓዘ ያለ ሰው ጭምር አረፍ እንዲል የመጋበዝ ድባብ አላቸው። የግራሩን ተፈጥሮ ይበልጥ በማጉላት ከአጠገቡ የተሰራው ፋውንቴንና ማረፊያ ስፍራዎች መንገደኛው ከድካሙ ነዋሪው ደግሞ በስፍራው አረፍ ብሎ እራሱን እንዲያዳምጥ ከወዳጆቻቸው፣ ከልጆቻቸው ጋር ለመወያየትና ለመዝናናት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
እዚህ ቦታ ላይ ከልጇ ጋር ቁጭ ብላ ያገኘናት አንዲት በሰላሳዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የምትገኝ እናትን ጠየቅናት፡፡ ቅድስት በሃይሉ ትባላለች። በሙያዋ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በአካውንታንትነት ትሰራለች። ወ/ሮ ቅድስት የምትኖረው ግንፍሌ ኮንዶሚኒየም መሆኑን በጨዋታ ጨዋታ ነግራናለች፡፡ ከዚህ ቀደም በተለይ እሁድና አልፎ አልፎ ከስራ መልስ ልጇን ይዛ ለመውጣት ታስብና ልጇ ግን የት ይዛው እንደምትሄድ ግራ ይገባት እንደነበር አጫውታናለች፡፡ “ቶሎ ወደ አዕምሮዬ ይመጣ የነበረው እሁድ ከሆነ አምባሳደር ቴአትር ቤት ጎን ያለው አምባሳደር መናፈሻና እንደተለመደው ወደ ካፌ ይዞ መሄድ ነበር፡፡ አሁን እየተሰሩ ያሉት የመዝናኛ አማራጮች ግን በተለይ ከልጆች ጋር መዝናናትና በእግር መንሸራሸር ለሚሹ አዲስ አበቤዎች ጥሩ አማራጭ ናቸው” ስትል ወ/ሮ ቅድስት አጫውታናለች፡፡
እነዚህን ፋውንቴኖችና ምቹ ማረፊያ ስፍራዎች አዲስ አበባን ምቹ ከተማ እንድትሆን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ያጫወተችን ወ/ሮ ቅድስት፣ “የከተሞች ዕድገት አንዱ መለኪያም ለነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጮችን ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ባቦጋያ፣ ሶደሬና ላንጋኖ ሰው በብዛት ይሄድ የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ የሌሉ የመዝናኛ አማራጮችን በመፈለግ ነው። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ የመዝናኛ አማራጮች እነዚህን ክፍተቶች የሚሞሉ ናቸው” ብላለች፡፡
በሌሎች ሀገራት ውስጥ እንደሚታየው ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች መዝናኛን በማቅረብ ውብ ከተሞች ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። ውብ ከተሞች ለመዝናኛ የሚያበረክቱት አንድ ጠቃሚ አስተዋፅዖ ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶችን የሚስቡ ድንቅ ምልክቶች እና መስህቦች በውስጣቸው መያዛቸው ብቻ አይደለም። ከዚያም ባሻገር፣ ውበት የተላበሱ ጎዳናዎች፣ ለአይን ማረፊያ የሚሆኑ ስፍራዎች፣ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎትና ልዩ ልዩ የመዝናኛ አማራጮችም ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ ሚናቸው ትልቅ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም ለሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ ጎብኚዎች ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ እየሆኑ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባን ገጽታም እየቀየሩት ነው፡፡ ይህንን አስተዋጽኦ ለመመልከት በእነዚህ አካባቢዎች ዞር ዞር ብሎ ቅኝት በማድረግ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ፍሉኢድራ የተባለ ገጸ-ድር በታህሳስ 2022 “The top 3 benefits of water fountains in urban innovation and development” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ፣ በከተማ ልማት ሂደት ውስጥ ፋውንቴኖችን መስራት ሦስት ዋና ዋና ጥቅሞች እንዳላቸው ዘርዝሯል፡፡ የመጀመሪያው ጠቀሜታ ቦታን ማስዋብ ሲሆን፤ ፋውንቴኖችን በአደባባዮች፣ በፓርኮች እና በሕዝብ መናፈሻ አካባቢዎች መስራት የሰዎች ልብ ውስጥ ተፈጥሮን የማድነቅና የመውደድ ስሜት ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ፋውንቴኖች ለእይታ የሚመቹ፣ በስራ የዛለውን ስሜት የሚያነቃቁና እረፍት ለማድረግ የሚመቹ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ፋውንቴኖች አካባቢያችንን ለማስዋብ ጉልህ ጠቀሜታ አላቸው ይላል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ፋውንቴኖች ምቹ የአየር ጸባይ የመፍጠር ጠቀሜታ አላቸው ይላል፤ ፍሉኢድራ ገጸ-ድር፡፡ የከተማ መስፋፋት በአካባቢው የሙቀት መጠን መጨመርን ሊያስከትል ይችላል። ፋውንቴኖች ደግሞ ይህን መሰል ሙቀት በመቆጣጠር ሚዛናዊ የአየር ሁኔታ በአካባቢያችን እንዲኖር የማድረግ አቅም እንዳላቸው መረጃው ይገልጻል፡፡ የፋውንቴኖች ሦስተኛ ጠቀሜታ ደግሞ የቱሪስት መስህብነታቸው ነው፡፡ ለዕይታ ምቹና ውብ የሆኑ የከተማ ፋውንቴኖች ቱሪዝምን እና የከተማዋን ዕሴት በማጉላት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ይሰጣሉ ሲል ፍሉኢድራ ገጸ-ድር አስነብቧል። ለአብነትም በሮም የሚገኘው ትሬቪ ፋውንቴን፣ የላስ ቬጋሱ ቤላጂዮ ፋውንቴን እና የባርሴሎናው ሞንትጁይክ ፋውንቴኖች ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው ሲል ይኸው ገጸ-ድር አክሏል፡፡
ሌላው የአዲስ አበባ ውበትና መዝናኛ እየሆኑ ካሉ አዳዲስ ፋውንቴኖችና ምቹ ማረፊያ ስፍራዎች መካከል፣ ፒያሳ ላይ የተሰራው የዓድዋ ሙዚየም መታሰቢያ ፊት ለፊት፤ ማለትም አራዳ ህንጻ ጎን ያለው ፋውንቴን አንዱ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ በተለይ ከሰዓት በኋላና አመሻሽ ላይ በርካታ ሰዎች የሚዝናኑበት ስፍራ ነው። ወጣቶች በጋራ ቁጭ ብለው ሲያወጉ፣ በጋራ ፎቶ የሚነሱና ከልጆቻቸው ጋር የሚዝናኑ አዲስ አበቤዎችን መመልከት እንግዳ አይደለም፡፡
ፒያሳ አራዳ ህንጻ እየተባለ በሚጠራው ህንፃ ጎን ባለው ፋውንቴን በጋራ ፎቶ ከሚነሱ ወጣቶች አንዱን ቀረብ ብለን አነጋገርነው፡፡ ናሆም ሃይሌ ይባላል፡፡ የኮሌጅ ተማሪ ሲሆን፣ የሚኖርበት ሰፈር ደግሞ አስኮ ነው፡፡ ወጣት ናሆም አሁን ላይ ፒያሳ ያከለቻቸው አዳዲስ ውበቶችና የመዝናኛ አማራጮች ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ “መዝናናት ማለት የሆነ ክለብና ባር ሄዶ መጠጣት ብቻ አይደለም። በመጠጣት የሚዝናኑ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ መብታቸው መሆኑን ስለምገነዘብ የመዝናኛ አማራጫቸውን አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን እንደእኔ ላሉ ወጣቶችና የመጠጣት ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም ብዙም የመዝናኛ አማራጮች አልነበረንም፡፡ ግፋ ቢል ካፌዎች ብንሄድ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን እንዲህ አይነት ፋውንቴኖች፣ በእግር ለመንሸራሸር የሚያስችሉ ውብ ጎዳናዎችና አረፍ ብሎ ለመጨዋወት የሚያስችሉ ማረፊያ ቦታዎች መሰራታቸው ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለከተማዋም ጭምር ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው” ሲል ወጣት ናሆም አጫውቶናል፡፡
የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም መግቢያ አካባቢ ባለው የማረፊያ ስፍራ ከስድስት ዓመት ሴት ልጁ ጋር ቁጭ ብሎ ሲዝናና ያገኘነው አቶ አንዋር ሙሰማም በአካባቢው ውሃ እየተራጩ ወዲህና ወዲያ የሚሯሯጡትን ልጆች በጣቱ እየጠቆመ፤ “ይሄ ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ልጆች በዚህ ልክ ሲደሰቱና ለአይናቸው የሚማርክ ነገር ማየታቸው ትልቅ ነገር ነው” ሲል አዲስ እየተሰሩ ያሉ ፋውንቴኖችና የመዝናኛ አማራጮች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለቸው ነግሮናል፡፡
ሌላው ለመዲናዋ አዲስ እይታን ከፈጠሩ ስፍራዎች መካከል አንዱ አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጎን የተሰራው ፋውንቴንና ማረፊያ ቦታ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ማረፊያ ወንበሮች፣ ማራኪ አበባዎች፣ እጅግ የሚያምር ፋውንቴን ተሰርቷል። ስፍራው ለአራት ኪሎ አዲስ እይታና ውበት አላብሶታል፡፡ ሰዎችም በአካባቢው አረፍ ብለው ሲጨዋወቱ፣ ፎቶ ሲነሱ፣ ቡና ሲጠጡና በተመስጦ ቁጭ ብለው የሚያስቡ ሰዎች መመልከት ይቻላል፡፡
ከሰሞኑ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት የሆነው የካዛንችስ የኮሪደር ልማትም የከተማዋ ሌላኛው መልክ ሆኖ መጥቷል፡፡ እጅግ ውብ የሆኑ የመዝናኛ አማራጮችና ሌሎችም አገልግሎቶችን አካትቶ የመጣው የካዛንችስ የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ገጽታ አንድ እርከን ከፍ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ በቀጣይ በተለይ በመዝናኛውና በቱሪዝም ዘርፍ ለከተማዋ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥር ፕሮጀክት መሆኑንም ተገልጿል፡፡
ዩር ፋውንቴንስ ኤክስፐርት የተሰኘው ገጸ-ድር በፈረንጆቹ መስከረም 21 ቀን 2024፣ “The Role of Fountains in Sustainable Urban Design” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ፣ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ ባሉበት እና ዘላቂ ልማት አሳሳቢ ጉዳይ በሆነበት ዘመን፣ ከተማን ማስዋብ፣ ማዘመንና የከተሞች አካባቢን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንደ ቅንጦት መታየት የለበትም ሲል ያስገነዝባል፡፡ ብዙውን ጊዜ የውበት እና የቅንጦት ምልክቶች ተደርገው የሚወሰዱ ፋውንቴኖች ቀጣይነት ላለው ጤናማ የከተማ ዲዛይን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚያትተው ገጸ-ድሩ፣ ፋውንቴኖች ለከተሞች ሥነ-ምህዳር፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ሲል መረጃው አክሏል፡፡
ከላይ ያሉትን ለአብነት ጠቀስን እንጂ ቀበና አደባባይ አካባቢ፣ አራት ኪሎ ሐውልቱ አጠገብ፣ የብልጽግና ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት አጠገብ እና እንዲሁም ሜክሲኮና ሌሎች አካባቢዎች የተሰሩ ፋውንቴኖች ከመዝናናት ባለፈም የመዲናዋን ገጽታ በመቀየር ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡