የመዲናዋን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅ አስጎብኚዎች ምን ያህል ሚናቸውን እየተወጡ ነው?

ማቴዎስ እሸቴ ይባላሉ፡፡ የማርገብ ቱር ኤንድ ትራቭል ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በተሻለ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ቱሪስቶችን ለመሳብ እና ለማቆየት የሚያስችሉ በርካታ ተጨማሪ ስራዎች መሰራታቸው ደግሞ ለቱሪዝሙ ትልቅ አበርከቶ አለው፡፡

ከዚህ በፊት ወደ ሀገር የምናመጣቸው ወይም የምናስጎበኛቸው ቱሪስቶች አብዛኛውን ጊዜ አዲስ አበባ ገብተው ነበር የሚወጡት፡፡ አሁን ግን በከተማዋ የተሰሩ ሙዚየሞችንና ፓርኮችን እንዲሁም ጎዳናዎችን እናስጎበኛቸዋለን፡፡ አዲስ ፕሮጀክት ሲመረቅ የጉብኝት ዝርዝራችን ውስጥ በማካተት ቱሪስቶችን ለማቆየት እና ከተማዋንም ራሳችንንም ለመጥቀም የሚያስችሉ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ ያብራራሉ፡፡

አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ይህንን ጉዳይ በውል እንረዳለን የሚሉት አቶ ማቴዎስ፣ የተሰሩትን አዳዲስ ፕሮጀክቶች በአግባቡ በማወቅ እና ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ በኩል የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እየተወጣን ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

የቱሪዝም መዳረሻን ማስተዋወቅ የቱሪስቶችን ቁጥር ለማብዛት አበርክቶው ትልቅ ነው

ለዚህ ማሳያ ሲጠቅሱም ቱሪስቶች ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ አይቆዩም ነበር። ብዙ ጊዜ ቆዩ ከተባለም አንድ እና ሁለት ቀን ብቻ ነበር የሚያድሩት፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ እንደ አሁኑ ምሽት ላይ ብርሃናማ አልነበረችም። ለእግር ጉዞ አትመችም ነበር፡፡ እንደ እንጦጦ እና አንድነት ፓርክ የመሳሰሉት መናፈሻዎች ብዙ አልነበሩም፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ገና አልተሰራም ነበር። ስለዚህ ቱሪስቶች እንደ መሸጋገሪያ ብቻ ነበር የሚጠቀሙባት፡፡ አሁን ግን ይህ ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡

አቶ ማቴዎስ አሁን እኛ ብቻም ሳይሆን ራሳቸው ይጠይቃሉ፡፡ ለአብነትም እንጦጦ እንድንወስዳቸው ይጠይቁናል። ምክንያቱም ከወትሮው የተለየ የሰዎች እንቅስቃሴና መዝናኛዎች አሉ፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ ሌሎች ስራዎችንም እያስተዋወቅን ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች ብዙ ተከታዮች አሉን፡፡ እርሱ ላይ አዳዲስና ነባር መዳረሻዎችን እናስተዋውቃለን፡፡ በዚህ ማስተዋወቅ ስራ ትኩረታችን የውጭ ቱሪስቶች ብቻ አይደሉም፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲስፋፋ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪዝም ቦታዎችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች እናስተዋውቃለን፡፡

አቶ ማቴዎስ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፣ የመዲናዋንም ሆነ የሀገራችንን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እንዲረዳ የአስጎብኚዎች ማህበር ተመስርቷል። በዚህም ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና ከቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በትብብር ይሰራሉ፡፡ አዳዲስ መረጃዎችን ይለዋወጣሉ፡፡ ይህም ሀገራችን ከቱሪዝም ለማግኘት ያቀደችውን ገቢም ሆነ ገጽታ ግንባታ እውን ለማድረግ ያስችላል፡፡

የማርገብ ቱር ኤንድ ትራቭል ስራ አስኪያጅ ማቴዎስ እሸቴ፣ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ከማንም የተሻለ እድል አለን፡፡ ብዙ ሀገራት ሄጃለሁ፡፡ ብዙ አቅም አለን፡፡ ሌሎች ሀገራት የሌላቸው እኛ ያለን ነገር ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ቀለም፣ ውበት፣ ተፈጥሮ እና ባህል አላት፡፡ አንዳንድ ሀገራት የዱር እንስሳት፣ አንዳንዶቹ ባህል፣ ሌሎቹ ደግሞ ቅርስ ብቻ አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሁሉም አለ፡፡ ይህንን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ እኛ ግን እንደ አስጎብኚ ድርጅት የሚጠበቅብንን እየሰራን ነው፤ ወደፊትም እንሰራለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ወንድይፍራው ግርማ ደግሞ  የዘርሲ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል መስራች እና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አቶ ወንድይፍራው በበኩላቸው፤ በክረምት ወራት በሀገራችን የጎብኚዎች እንቅስቃሴ ይቀንሳል፡፡ በመስከረም ግን ሁሉም ነገር ይነቃቃል፡፡ መስከረም ወር ትልቅ ወር ነው፡፡ ክረምቱ ሲወጣ ጉዞ ይጀመራል። በዓላት አሉ፡፡ ጎብኚዎች ይመጣሉ ብለዋል፡፡

አሁን ጥሩ መነቃቃት አለ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ የተሰሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡ አዲስ ዓመት እና ሌሎች በዓላትን አስታክከው የሚመጡ ጎብኚዎች የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ የማድረግ ስራ እያከናወንን ነው፡፡ እንጦጦ ፓርክን ጨምሮ በተለያዩ የመዲናዋ ክፍሎች የሚገኙትን የኮሪደር ልማቶች ለማስተዋወቅ የከተማ “Walking tourism” በሚል እየሰራን ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

አቶ ወንድይፍራው፣ በፊት ቱሪስቶች በብዛት አዲስ አበባን አይጎበኙም፤ በእግርም ብዙ አይጓዙም፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በመኪና ነበር የምናንቀሳቅሳቸው፡፡ አሁን ግን በእግራቸው እየተጓዙ እየተዝናኑ ከተማዋንም እያዩ እንዲሄዱ ነው የምናደርጋቸው፡፡ ለአብነትም ከመስቀል አደባባይ አስከ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የተለመደ የእግር ጉዞ እና መዝናኛ አለ፡፡ ይህ ለሀገር ውስጥም፣ ለውጭ ጎብኚዎችም የምናደርገው ነገር ነው፡፡ በተቻለን አቅም አዳዲስ መዳረሻ ከተማዋ ላይ ሲሰራ ቶሎ በመረዳት እና ለጎብኚዎች መረጃ በመስጠት የመዳረሻ አካል የማድረግ ስራ እየሰራን ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድና የራሷን በማጋራት ዘርፉን ማሳደግ አለባት የሚሉት ስራ አስኪያጁ በቱሪዝም ላይ ከሌሎች ሀገራት በተለይ ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር ልምድ እንለዋወጣለን። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተለያዩ ሀገራት ቋንቋ የአዲስ አበባን ጨምሮ የሌሎችን አካባቢዎች መዳረሻዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ዘመኑ የዲጂታል እንደመሆኑ ይህንንም በስፋት እየሰራንበት ነው ብለዋል፡፡

ቱሪስቶች አዲስ ነገር ይፈልጋሉ የሚሉት አቶ ወንድይፍራው፣ ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ በየወቅቱ የሚሰሩትን የመዝናኛ ስፍራዎች በማስታወቂያ ስራችን እናካትታለን፡፡ ቱሪዝም ሚኒስቴርም የተለያዩ ዝግጅቶችን ያዘጋጃል፤ በተቻለ አቅምም ድጋፍ ያደርግልናል፡፡ ይህ ደግሞ የመዲናዋን አዳዲስ መዳረሻዎች በተቀናጀ መንገድ ለማስተዋወቅ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህም ቱሪስቶች ለአዲስ አበባ ያላቸው እይታ እና አመለካከት እንዲቀየር አድርጎታል፡፡ ስለዚህ ብዙ ሀገራትን የሚያዳርሰው አየር መንገድን ጨምሮ፣ አስጎብኚዎች ጥረት በማድረግ ብዙ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችንና ከተማችን በአንድ ጊዜ በሚመጡበት (Mass tourism) ላይ መስራት አለብን ፡፡

በተለይ አሁን የዓድዋ ድል መታሰቢያ አለ፡፡ ታሪክ ነው፡፡ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ እንጦጦ ፓርክ… ለአዲስ አበባ ሌላ ውበትን ጨምረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ መሸጋገሪያ ሳትሆን የምትጎበኝ ከተማ መሆኗን ያሳየ ነው። አዳዲስ መዳረሻዎች ሲጠናቀቁ በፍጥነት በማስተዋወቅ ለጎብኚዎች በምናዘጋጀው የመዳረሻ ዝርዝር ውስጥ እያካተትን ነው፡፡ በእግር ከመሄድም ባለፈ በክፍት መኪናዎች እየተዟዟሩ የሚጎበኙበትን እድልም ማሳደግ ይገባናል፡፡ ከዚህም በላይ የቱሪስቶችን ቆይታ ማሳደግ አለብን ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ  የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሃገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አይናቸው በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተሰሩና በመሰራት ላይ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና መዲናዋ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችሉ ስራዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንሰራለን። ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከል ቀዳሚ ተጠቃሾቹ አስጎብኚ ድርጅቶች ናቸው ይላሉ፡፡

ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እንሰራለን፡፡ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ አስብኚዎች ጋር መረጃ በመለዋወጥ እና በመተጋገዝ እንሰራለን፡፡ አስፈላጊ ሲሆን እኛም ወደ እነርሱ እንሄዳለን፡፡ እነርሱም ወደእኛ ይመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ዋና አላማው የከተማዋን ቱሪዝም ማሳደግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የመዲናዋን አዳዲስ ፕሮጀክቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ ከአስጐብኚ ማህበራትና ድርጅቶች ጋር የትብብር ሰነድ በመፈራረም ጭምር አብረን እየሰራን ነው ሲሉ አቶ ሳምሶን  አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቱሪዝሙ ዘርፍ እየሰራችው ያለችው ስራ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ እውቅናን እያገኘ ነው፡፡ ለአብነትም በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢጋድ የቱሪዝም ሻምፒዮን ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የቱሪዝም ሻምፒዮን እንዲሆኑ አባል ሀገራቱ የቱሪዝም ሚኒስትሮች ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለራዕይ መሪነት በቀጣናው ቱሪዝምን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ኢጋድ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር በኢጋድ አባል ሀገራት ዘንድ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት፣ ቅርሶችን እና አካባቢን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ማስገንዘቡ የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ሻምፒዮና ሆነው እመርታዊ ለውጥ እንዳስመዘገቡት ሁሉ ለቀጠናው የቱሪዝም ሻምፒዮን በመሆን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጠናከር እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት በቱሪዝም ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም በወቅቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review