አሽከርክር ረጋ ብለህ፣
አትቸኩል ትደርሳለህ ዘና ብለህ… የሚሉ ስንኞች ለአብዛኛው ሰው እንግዳ አይደሉም፡፡ ሙዚቃውን በርካቶች ያስታውሱታል፤ ስለትራፊክ ከተዘፈኑ ዘፈኖች ውስጥ ጥቀሱ ቢባሉ ቀድመው ሊጠሩት የሚችሉት ሙዚቃ ነው፡፡ “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የተሰኘው ሙዚቃ “ቡና ቡና” እንደሚለው መዝሙር ሁሉ ከበርካቶች አዕምሮ የማይጠፋ ጥልቅ መልዕክት ያለውና ዛሬም ድረስ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሚደመጥ ነው፡፡ ሙዚቃ የማይረሳ፣ እያዝናና መልዕክት የሚያስተላልፍ፣ በአጭር ደቂቃ ብዙ ግንዛቤ መፍጠር የሚችል ጥበባዊ ስራ ነው፡፡ “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የሚለው ሙዚቃም ዛሬም ድረስ የበርካታ የትራፊክ ዘገባዎች ማጀቢያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከአፋን ኦሮሞ ከተሰሩ የትራፊክ የሙዚቃ ስራዎች ደግሞ “SUUTAA SUUTAA (ሱታ ሱታ)”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በነገው እለት የሚከበረውን “ዓለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን” መነሻ በማድረግ በሀገራችን የትራፊክ አደጋ ግንዛቤን ለማሳደግ ከተሰሩ ሙዚቃዎች ውስጥ የተወሰኑትን የግጥም ይዘትና መልዕክት በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡
ሙዚቃ እና የመንገድ ትራፊክ
በቅርብ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ሙዚቃ አሽከርካሪዎችን በማነቃቃት እና ግንዛቤ በመፍጠር የትራፊክ አደጋን ይቀንሳል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡
ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ሃያሲው ዋለልኝ አየለ በበኩሉ ሙዚቃ ሰዎችን ለማስተማር እና ግንዛቤ ለመፍጠር ያለው ከፍተኛ አቅም የሚያጠያይቅ አይደለም ይላል። በሀገራችን እጅግ በርካታ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሙዚቃዎችና ህብረ ዝማሬዎች ተሰርተዋል፡፡ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እና የመንገድ ደህንነት ግንዛቤን ለማሳደግ ጥሩ ግጥም፣ በልቦና የሚቀረጽ ዜማ እና የማይረሳ መልዕክት ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በቀዳሚነት መጠቀስ ከሚችሉት የሀገራችን ሙዚቃዎች ውስጥ በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የሚለው ነው፡፡
ይህ ሙዚቃ ግጥሙ የተጻፈው በሞገስ ተካ እና ይልማ ገብረአብ ነው፡፡ ዜማውን የደረሰው ሞገስ ተካ ነው፡፡ በሙዚቃው ላይ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ግርማ ተፈራ፣ ምናሉሽ ረታ እና ሞገስ ተካን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች ተሳትፈውበታል፡፡
ሁሌም ረጋ ብለን፣ በትዕግሥት እንንዳ
ሕይወት እንዳንቀጥፍ፣ አካል እንዳንጎዳ
አሽከርክር ረጋ ብለህ፣
አሽከርክር ትደርሳለህ፣ ረጋ ብለህ!
ትዳርህን አስብ! ትዳርሽን አስቢ
ልጆችህን አስብ ልጆችሽን አስቢ… ይላል፡፡
“አሽከርክር ረጋ ብለህ” የሚለው ጥበባዊ ስራ በእዝነ ልቦና የሚታወስ፣ የማይረሳ፣ የትራፊክ ደህንነት የሬዲዮም ሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በመግቢያነት (Intro) የሚቀርብ ዜማ ወይም መዝሙር ነው፡፡ የሙዚቃው ስንኞችም ሰፊ መልዕክትን የያዙ ናቸው፡፡ በተለይም በመነሻ ላይ ያለው አዝማች ሕይወት በከንቱ በመኪና አደጋ እንዳይጠፋ በእርጋታ እና በትግዕስት የማሽከርከርን ተገቢነት አበክሮ ያስገነዝባል፡፡
ከባድ ሃላፊነት እንዳለብን አውቀን
ሁልጊዜም ስንጓዝ ይሁን ተጠንቅቀን… እያለ ሙዚቃው ይቀጥላል፡፡ ለትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ውስጥ አንዱ ፍጥነት ነው። በርካታ ሹፌሮች ፍጥነትን፣ በአጭር ደቂቃ ሩቅ ቦታ መድረስን የችሎታ መለኪያ ያደርጉታል። ይህ የጥበብ ስራ ግን ስክነት እንጂ ፍጥነት ጠቃሚ አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
መፍጠንና መቅደም አይደለም ችሎታ
ትዕግስት እንላበስ ይኑረን እርጋታ… በማለት ጠቁሟል፡፡
ከትራፊክ ህግና መርሆች ውስጥ አንዱ ርህራሄ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእግረኛ ቅድሚያ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ ለሴቶችና ህጻናት መጠንቀቅን ያካትታል፡፡ የጥበብ ስራው ይህን መሰረታዊ የአሽከርካሪዎች ግዴታና ሃላፊነት ይጠቅሳል፡፡
ለእግረኛ ቅድሚያ እንስጥ በየመታጠፊያው
አደጋው ይቀንስ የሰው ህይወት መጥፊያው
ሴቶችና ህጻናት አረጋዊያኑ
በመኪና አደጋ ከማለቅ ይዳኑ
አሽከርክር ረጋ ብለህ
አትቸኩል ትደርሳለህ ዘና ብለህ… በማለትም በጥቂት ሰዓትና ደቂቃ ትዕግስት ማጣት፣ የማይተካ የሰው ልጅ ውድ ህይወት ማለፍ የለበትም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሸከርካሪዎች አላሰፈላጊ ባህሪያት የሚባሉት ሞገደኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ አለመረጋጋት፣ ቸልተኝነት፣ ትኩረት ለመሳብ መሞከር (ልታይ ልታይ ባይነት)፣ ሃላፊነትን መዘንጋት እና ሱሰኝነት ናቸው፡፡ አንጋፋዎቹ የሀገራችን አርቲስቶች እያሽከረከርን እንዳንዘናጋ ሙያቸውን በመጠቀም፣ እያዝናና በሚያስተምር እና በማይዘነጋ ጥበባዊ ስራቸው፣ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት እንደሚከተለው ማስተላለፍ ችለዋል፡፡
በቸልተኝነት ይደርሳል አደጋ
አይገኝምና ህይወት እንደዋዛ
መቼም ይሁን የትም ለህግ እንገዛ
ከአልኮል ከአንደዛዥ ዕፅ ከሱስ ሁሉ ጸድተን
ድካም እናስወግድ በቂ እንቅልፍ ተኝተን
ፋታ ያጣ ሹፌር ሁሌም ይዘናጋል
ሰላማዊ ኑሮን በድንገት ያናጋል፡፡
በለጠ አለነ የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መንገድ ፈንድ አገልግሎት የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አዘጋጅ ነው፡፡ ጉዞ እና እንደርሳለን የተሰኙትን ታዋቂ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ለዓመታት አዘጋጅቷል፡፡ ኪነ ጥበብ ብዙ ነገሮችን ይለውጣል፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የተሰሩ ሙዚቃዎች በልባችን ውስጥ ቀርተዋል፤ ትራፊክን በተመለከተም “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የተሰኘውን ስራ መጥቀስ ይቻላል፤ እነዚህም ሳቢና አስተማሪ ናቸው ይላል፤ አሁንም በጭውውት፣ በሙዚቃና በተለያየ መልኩ አሳሳቢ የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በኪነ ጥበብ ብዙ ነገሮችን መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲልም በለጠ ያክላል፡፡
የትራፊክ ፕሮግራም አዘጋጁ በለጠ የጠቀሰው ሌላኛው ሙዚቃ “ሰከን ሰከን” የሚለውን ነው፡፡ ይህ ታዋቂ የትራፊክ ሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲው አማኑኤል ይልማ ነው። ድምጻዊ ታምራት ደስታ፣ ዳን አድማሱ እና ጌትሽ ማሞን ጨምሮ ሌሎች አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎችም የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህ ሙዚቃ
ሰከን ሰከን ቀስ ቀስ
የወገን ደም በከንቱ እንዳይፈስ
የማሽከርከር ብቃት ልምዱ
ከሌላችሁ ከቶ አትንዱ
ከአደንዛዥ ዕፅ ከአልኮል ርቀን
እናሽከርክር ተጠንቅቀን… እያለ በጥሩ ዜማ እና በቅብብሎሽ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡
የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ለቅድመ መከላከል ግንዛቤ ሊሰጡ የሚያስችሉ መዝሙሮችና ሙዚቃዎች በተለያየ ቋንቋ ተሰርተዋል፡፡ እንዲያውም ከህዝብ ብዛትና እየደረሰ ካለው የትራፊክ አደጋ አንጻር የተሰሩት የሙዚቃ ስራዎች እጅግ ትንሽ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ኪነ ጥበብ ለማህበራዊ እድገትና ለውጥ ትልቁን ሚና መወጣት አለባት የሚለው ገጣሚ ዋለልኝ ግጥሞችንና ሙዚቃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች በብዛት መስራት የህዝቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ የሚደርሰውን አደጋ ማስቀረትና ለለውጥ እና እድገት ማነሳሳት ይቻላል ይላል። በሀገራችን ስለመንገድ ትራፊክ ከተሰሩና ተወዳጅነትን ካተረፉ ሙዚቃዎች ውስጥ አንዱ በአፋን ኦሮሞ የተሰራው “SUUTAA( ሱታ ሱታ) ዋነኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ ሱታ ሱታ መዝሙር በበርካቶች ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡ይህ ሙዚቃም ቀስ ብለህ አሽከርክር የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ ይህ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃው ወደየትም ብትሄድ ዋናው ሰላም መድረስህ ነው። ሰላም የምትደርሰው ደግሞ ፍጥነትህን ቀንሰህ እና ተጠንቅቀህ ስታሽከረክር ነው የሚል ጥቅልና ጥልቅ መልዕክትን ይዟል፡፡
ሌላው “እባካችሁ” የተሰኘው ህብረ ዝማሬ ይጠቀሳል፡፡የዚህ ሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲ ሰለሞን አድማሴ ነው፡፡ይህ ህብረ ዝማሬ ዋና ትኩረቱን ልጆች ላይ የሚደርስ የትራፊክ አደጋን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ ህብረ ዝማሬው የተዜመውም በልጆች አንደበት ነው፡፡
እባካችሁ እባካችሁ
ለእናት ሀገር ለእኛ ብላችሁ
የምሽት ከዋክብት ብርሃን ጮራችሁ
የአካላችሁ ከፋይ ሆነን ልጆቻችሁ
እኮ ለምን
ያልጠነከረ አካል የሟሸሸ ስጋ
ጠፍቷል እንደ ድንገት በመኪና አደጋ
በቸልተኝነት በማሽከርከራችሁ
የስንቱን ታዳጊ ህይወት ቀጠፋችሁ… በሚል ጥልቅ መልዕክት፣በጠንካራ ቃላትና ልብ በሚነካ ስንኝ የተሰራ ነው፡፡
ህብረ ዝማሬው በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የታዳጊዎችን ህይወት ለሚቀጥፉና ለአካል ጉዳት ለሚዳርጉ አሽከርካሪዎች ጥብቅ መልዕክት ተላልፎበታል፡፡
መልካም ስራችሁን እንድንሆን ወራሽ
አታድርጉን እኛን የሙት ገፈት ቀማሽ
እሪታ ዋይታ መጮህና ማልቀስ
ፍጹም አያድንም ነገን ከመውቀስ
እባካችሁ እባካችሁ
የእናንተው ነን የእኛው ናችሁ፡፡
ጋዜጠኛ እና ገጣሚ ዋለልኝ የኪነ ጥበብ ሰዎች ለአሽከርካሪዎች ግንዛቤ ማሳደጊያ ከሚሰሯቸው ሙዚቃዎች እኩል ልጆች ላይ ትኩረት አድርገው ቢሰሩ፣የግጥሙ ይዘትም እነሱን ያማከለ ቢሆን የሚል ሃሳብ አለው፡፡ ምክንያቱም ልጆችን በመዝሙርና በሙዚቃ ስለመንገድ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ አድገው ሹፌር የሚሆኑት እነርሱ ናቸው፡፡ ትልቅ ሰው ሲሆኑ በመንገድ ላይ ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱት እነርሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለልጆች በትምህርት ገበታ፣ በመዝሙር፣በሙዚቃ፣በፊልም፣በተረት ማስተማር ይገባል፤የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ላይ መሰል የኪነ ጥበብ ስራዎችን እመለከታለሁ ሲል የማጠቃለያ አስተያየቱን አጋርቷል፡፡
በኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ለህጻናት ስለመንገድ አጠቃቀምና የትራፊክ አደጋ ለማስተማር የተሰራው መዝሙር ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዩቱዩብ ብቻ ተመልክተውታል። ልጆችን እያዝናና የሚያስተምረው ይህ መዝሙር መልዕክቱ በተለይ በአዲስ አበባ ከሚስተዋለው ትክክለኛ ያልሆነ የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ልማድ አንጻር ለአዋቂዎችም የሚሆን መዝሙር ነው፡፡
አስፋልት ሲሻገሩ ያልተጠነቀቁ
ግራ ቀኝ ያላዩ ህግን ያልጠበቁ
በመኪና አደጋ ይታያል ሲጠቁ
ራስን ለማዳን ሰዎች ተጠንቀቁ…እያለ ይቀጥላል፡፡
የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በኪነ ጥበብ የታገዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በሀገራችንም በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ የተሰሩትና እየተሰሩ የሚገኙት ምቹ መንገዶች፣የትራፊክ መብራቶች፣የእግረኛ መንገዶችና ማቋረጫዎች የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ትልቅ ድርሻ አላቸው።
በጊዜው አማረ