የሚሰሩ ስራዎች ለትውልድ የሚተላለፉ አሻራዎች እንዲሆኑ ተደርገው ሊሰሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች 120 አመታትን ያስቆጠረውን እና የታደሰውን የድሮውን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መርቀዋል።
የዛሬ አራት አመት እድሳቱ የተጀመረውና በአርቲስት አለምጸሀይ ወዳጆ ለተመሠረተው ጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የተደረገው የቢተወደድ ሀይለ ጊዮርጊስ ወልደሚካኤል ቤት፣ በከተማዋ ከሚገኙ ውብ ኪነ ህንጻዎች አንዱ ነው።
ቤቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ በጥንካሬ መቆየቱ፣ ለትውልድ የሚተላፍ ሆኖ በመገንባቱ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የምንሰራቸው ስራዎች ዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን ትውልድ ጭምር ታሳቢ አድርገን መስራት እንዳለብን የምንማርበትም ነው ብለዋል።
የፒያሳ አካባቢ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፣ እነዚህን ቅርሶች የማደስ እና የማስዋብ እንዲሁም ጎልተው እንዲወጡ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ተግባር አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት፡፡
ማዕከሉ፣ ትውልድ የሚታነጽበት በመሆኑ አንጋፋ የኪነ ጥበብ እና የባህል ባለሙያዎች ልምዳቸውን እና እውቀታቸውን በማካፈል ትውልድ እንዲቀርጹበትም ከንቲባ አዳነች አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ቅርሱን እንዲጠቀምበት ከማስረከብ ባለፈ፣ የ39 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ ደረጃውን ጠብቆ እንዲታደስ ላደረገው ድጋፍም የማዕከሉ መስራች አርቲስት አለምጸሀይ ወዳጆ ምስጋና አቅርባለች።
በሰብስቤ ባዩ