
ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የምክክር ሂደትን ባህል ለማድረግ እየተካሄደ ባለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) አስታወቁ ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር ነገ በሆሳዕና ከተማ የውይይት መድረክ ያካሂዳል።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እያካሄደ ያለው የምክክር ሂደት እስከ አአሁን ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር ቁልፍ የሆነውን የምክክር ሂደት ባህል ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በ11 ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሀገራዊ የምክክር ሂደትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ለሀገራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የምክክር ሂደትን ባህል ለማድረግ እየተኬደ ባለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነገ የሚካሄደው የምክክር መድረክ ኮሚሽኑ እስከ አሁን ድረስ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን ለባለድርሻ አካላት ለማሳወቅ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በምክክር መድረኩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወኪሎችና የሃይማኖት መሪዎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና እድገትን ለማረጋገጥ በኮሚሽኑ የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በሀገር ደረጃ የኖረውን የአብሮነትና የመተባበር እሴት በማጎልበትና በማህበረሰቡ ዘንድ በማስረፅ የመገናኛ ብዙሃን እያከናወኑ ያለውን ተግባር ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።