
AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም
የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በአገራዊ የሰላም ግንባታ ስራዎች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሀመድ እድሪስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሀገራችንን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ምክክር አድርገዋል፡፡
ቤተ-ክርስቲያኗ ከመንግስት ጋር በመደጋገፍና በመቀራረብ በሰላም ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋትና በመቀራረብ እንደምትስራ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አረጋግጠዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ለትውውቅና ለውይይት ወደ መንበረ ፓትሪያርክ በመምጣታቸውም አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ በበኩላቸው ቤተ-ክርስቲያኗ በሰላምና በሀገረ መንግስት ግንባታ ካላት የካበተና የዳበረ ልምድ በመነሳት የተጀመረው የሰላም ሂደት እንዲጎለብት እና ለሰላም ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ የበኩሏን ሚና ትወጣ ዘንድ ጠይቀዋል።
መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም የሚከፈል ዋጋን ለመክፍል ያለውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች ጋር በትብብርና በቅርበት እንደሚሰራም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡