የሰመራ ወደብና ተርሚናል ከባሕር ወደቦች ካለው ቅርበት አንፃር ስትራቴጂካዊ በመሆኑ ይበልጥ ሊለማ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በዋና ሥራ አስፈጻሚው ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፥ የተመራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በዚህም የወደቡን የኦፕሬሽን ስራዎች፣ የመሰረተ ልማት፣ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን እና አጠቃላይ የወደቡን ሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተው በቀጣይ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችም አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት የሰመራ ወደብ ከአጎራባች ሀገሮች የባሕር ወደቦች በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ እና ለሀገር ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ይበልጥ መልማትና ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ (ኢባትሎ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ማኔጅመንት ለኢባትሎ በሚያደርጉት ድጋፍ እንዲሁም ላደረጉት ጉብኝት አመስግነዋል።
የሰመራ ወደብና ተርሚናል 160 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን፣ 1 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሁለት እንዲሁም 800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው አንድ መጋዘን፣ እና 2 ነጥብ 5 ሄክታር የኮንቴይነር ማስተናገጃ ተርሚናል ላይ በመልቲሞዳል እና ዩኒ ሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት ተጓጉዘው ወደ ሀገር ለሚገቡ እና ከሀገር ለሚወጡ ጭነቶች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ከሰመራ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሚሌ ከተማ የአሽከርካሪዎች ማረፊያ እና የከባድ ተሽከርካሪዎች ጥገና መስጫ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።