
AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ አጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ።
ከሕዳር 27 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም “ለዘላቂ ሰላምና ፍትኃዊ ልማት ቃል ኪዳናችንን እናድስ” በሚል መሪ ኃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረውን አራተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሣምንትን በማስመልከት ባለሥልጣኑ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሣምንት ዓላማ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ላይ ያላቸውን አስተዋፅዖ ለማሳደግና ዘርፉን ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር ጠንካራ የእርስ በርስ ትስስር የሚፈጥሩበት አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው ከዚህ ቀደም ለሥራ አዳጋች የነበሩ ሕጎችና ደንቦችን ከመቀየር ጀምሮ በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ ምህዳር በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየሰሩ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሁን ላይ ቁጥራቸው ከ5 ሺህ በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥራቸው ብቻ ሳይሆን በዘላቂ ልማት፣ በሰላም ግንባታ፣ በግጭት አፈታት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል።
ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተከሰቱ ወቅትም የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዋና የሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በሽግግር ፍትህ፣ በሰላም ግንባታና በተለይም ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ከረቂቅ አዋጁ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
4ኛው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በፓናል ውይይት፣ በኤግዚቪሽንና በሌሎችም ዝግጅቶች እንደሚከበር በመግለጫው መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡