የሳይበር ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

You are currently viewing የሳይበር ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና የፍትሕ ሚኒስቴር የሳይበር ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትና ትግበራ፤ የኮምፒውተር ወንጀሎች ምርመራ፣ መረጃ አሰባሰብና ክስ ሂደት እንዲሁም በሕግ ጥናትና ረቂቅ ሕግ ዝግጅትና ተያያዥ የሳይበር ወንጀል መከላከል ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስምምነቱን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እና የፍትሕ ሚኒስትር ወ/ሮ ሃና አርአያሥላሴ ፈርመውታል፡፡

በሀገራችን የዲጂታላይዜሽን መስፋፋትን ተከትሎ በርካታ እና ውስብስብ የሳይበር ወንጀሎች መከሰታቸውና ወደፊትም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የሳይበር ወንጀል የመከላከል አቅማችንን በቀጣይነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም በሁለቱ ተቋማት መካከል ቀድመው የተጀመሩ የትብብር ሥራዎችን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

በሳይበር ወንጀል ሀገራዊ ማዕቀፎች እንዲሁም በሳይበር ወንጀል ምርመራ እና ዲጂታል ፎረንሲክን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ጠንካራ የሳይበር ወንጀል ምርመራ አቅም መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የፍትሕ ሚንስትር ወ/ሮ ሃና አርአያሥላሴ እንደገለጹት በሀገራችን የሚከሰቱ የሳይበር ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ከመሆናቸው አኳያ በወቅታዊነትም ይሁን በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የሳይበር ወንጀሎችን ለመመርመር፣ ማስረጃ ለማውጣት እና የፍትሕ ስርአት ማስፈን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሳይበር ወንጀል ምርመራ አቅም መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ኢመደአ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ በተቋሙ በነበራቸው ጉብኝት እንደተመለከቱ ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review