AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
የስንዴ ልማት ላይ እየታየ ያለው ክንውን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የኢንደስትሪ ግብዓትን በማስፋት እና ወጪ ንግድን በመጨመር ረገድ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የለውጡ መንግሥታችን፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር፣ የክልላችንን የኢኮኖሚ መዋቅር ዝንፈት ለማረቅ፣ ያለን ትልቁ አቅም ግብርና መሆኑን ተገንዘቦ ነው ወደ ሥራ የገባው ብለዋል።

በዚህ ረገድ፤ የስንዴ ልማት ላይ እየታየ ያለው ክንውን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የሀገር ውስጥ የኢንደስትሪ ግብዓት በማስፋት እና ወጪ ንግድን በመጨመር ረገድ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
ጅምሩን ለማስፈንጠር መንግሥት የግብርና ግብዓት እና ቴክኖሎጂ በማቅረብ፣ የአርሶ አደሩን ክህሎት በማሳደግ፣ የኢኮኖሚ መዋቅሩን በማስተካከል እና የንግድ ሥርዓቱን በማመቻቸት ረገድ በስፋት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

በስንዴ ልማት ዙርያ እየታየ የሚገኘው የስኬት ብልጭታ ያለንን እምቅ አቅም ከማስታወስ የዘለለ አይደለም ሲሉም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
የሴክተሩን ሁለንተናዊ ሽግግር እውን በማድረግ የወል እና የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ በግብርናው ዘርፍ መውሰድ የጀመርናቸውን ስትራቴጂካዊና የተቀናጁ እርምጃዎች አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን በየደረጃው ያለ አመራራችን የሚስተው ጉዳይ አይደለም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡