AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
የናሚቢያ አባት በመባል የሚታወቁት እና የናሚቢያ የነጻነት ምልክት ተደርገው የሚወሰዱት የመጀመሪያው የናሚቢያ ፕሬዝደንት ሳም ኑጆማ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ሳም ኑጆማ በሞቀ ፈገግታቸው እና ቀለል ባለ ማንነትም ይታወቃሉ፡፡
በስልጣን ላይ ያሉት የአገሪቱ ፕሬዝደንት ናንጎሎ ሙቡምባ ናቸው የቀድሞውን ፕሬዝደንት ዕረፍት ያወጁት፡፡
ፕሬዝደንቱ ‘የሳም ኑጆማ ሞት አስደንጋጭ ነው’ ብለዋል፡፡
ሳም ኑጆማ ናሚቢያ ከደቡብ አፍሪካው ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ እንድትወጣ ከፍተኛ ትግል እንዳደረጉ እና ትግሉንም እንዳስተባበሩ ይነገራል፡፡
አገሪቱ እ.አ.አ በ1990 ነጻ ስትወጣም የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን ሀገራቸውን እስከ እ.አ.አ እስከ 2005 መርተዋል፡፡
ከነጻነት በኋላ በአገሪቱ ብሄራዊ እርቅ በማድረግ ከነጮች ጋር አብሮ በሰላም መኖርን ያሳዩ በአገሪቱ ሰላም እና ጸጥታን በማስፈን ይታወቃሉ፡፡
የሴቶች እና ህጻናትን መብት ያረጋገጡ ናቸውም ይባላል፡፡
ሳም ኑጆማ ላለፉት 3 ሳምንታት በሆስፒታለ በህክምና ሲረዱ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
በቀድሞው ፕሬዝደንት ህልፈት የአለም አገራት በተለይም የአፍሪካ አገራት መሪዎች ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ስለ ስርዓተ ቀብራቸው ሁኔታ እስካሁን የተባለ ነገር አለመኖሩን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡