የበቃ ትውልድ ለማፍራት ብቁ እና ዘመኑን የዋጀ አሰልጣኝ ማፍራት ግዴታ ነው፡- የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን

AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም

የበቃ ትውልድ ለማፍራት ብቁ እና ዘመኑን የዋጀ አሰልጣኝ ማፍራት ግዴታ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ስራ እና ክህሎት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ቅንጅታዊ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሄደዋል።

አጫጭርም ሆነ መደበኛ ስልጠና የሚያገኙ ሰልጣኞች በገበያው ተፈላጊ እንዲሆኑ ጥራት እና አግባብነት ያለው ስልጠና በመስጠት የበቃ የሰው ሐይል ማፍራት አስፈላጊ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ስልጠና እና የተቋማት ልማት ዳይሬክተር አቶ አምባቸው ግርማይ ገልጸዋል።

የስልጠና ጥራት ጉዳይ አሁንም ትኩረት የሚሻ መሆኑንም አቶ አምባቸው ተናግረዋል ።

የውይይቱ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም በሰልጣኞች ምዘና ወቅት የስነ ምግባር ጉዳለት ያለባቸው መዛኞች በመኖራቸው ይህ ችግር እንዲቀርፉላቸው ጠይቀዋል።

በመድረኩም የበቃ ትውልድ ለማፍራት የበቃ አሰልጣኝ ማፍራት ግዴታ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ ገልጸዋል።

በመዛኞች ላይ የቀረበውን ቅሬታ ተከታትሎ ባለስልጣኑ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልፀው ፣ ጥራት ያለው ስልጠና መስጠት ከተቻለ ብቁ የሰው ሐይል ማፍራት አዳጋች እንደማይሆን ተናግረዋል።

በአዲሱ የሙያ ደረጃ መሰረት ስልጠና እየተሰጠ አለመሆኑን እና የትብብር ስልጠና አተገባበር በሚፈለገው ደረጃ ልክ አለመገኘቱ በውይይት መድረኩ ተገልጿል።

ተቋሙ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች እና በድንገተኛ ኢንስፔክሽን የተገኙ ግኝቶችን በቅርቡ ለማህበረሰቡ ይፋ እንደሚደረግ ባለስልጣኑ አሰወታውቋል።

በዳንኤል መላኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review