በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የፋሲካ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ዕለት በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በመጸለይ፣ በመስገድ፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን በመፈጸምና ትምህርቶችን በመስማት ያከብራሉ።
የ???ትንሳኤ ወይም የፋሲካ በዓል በተለያዩ ሀገራት የሚከበር ሲሆን በእየሩሳሌም፣ በሩሲያ፣ በቤላሩስ፣ በግሪክ፣ በሜቄዶንያ፣ በሞሎዶቪያ፣ እንግሊዝ፣ በጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን ከሚከበርባቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍም የተወሰኑ ሀገራትን የፋሲካ በዓል አከባበር ምን እንደሚመስል እንቃኛለን፡፡
የብራዚል የክርስትና እምነት ተከታዮች የፋሲካ በዓልን ማክበር የሚጀምሩት በዘንባባ ዝንጣፊ የሚደረግ ቡራኬን በማካሄድ ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስንና የቅድስት ማሪያምን ሀውልት ተሸክመው በአደባባይ በመዞርም ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ያካሂዳሉ፡፡ ሰሞነ ህማማት ሲጀምር በዓሉን በደስታ የሚቀበሉት ብራዚሎች ተከትሎም ልዩ ልዩ የደስታ ድግሶችንም ያካሂዳሉ፡፡ በፋሲካ ሰሞን ንስሃ መግባትም በብራዚል የተለመደ ነው፡፡ በፋሲካ ዕለት ምዕመናን አበባዎችን በየቤተ ክርስቲያኑ ይዘው በመሄድ ከንስሃ አባቶች ልዩ ቡራኬን ይቀበላሉ፡፡

በሜክሲኮውያን ዘንድ ደግሞ የሆሳዕና ዕለት የክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም መምጣት በዘምባባ ዝንጣፊ ደምቆ ይከበራል፡፡ በየቤተ ክርስቲያኑ በመገኘት የዘንባባ ዝንጣፊ በማድረግ ሰሞነ ህማማትን የሚቀበሉት ሜክሲኮዎች ንስሃ በመግባትና በጸሎት ጭምር የበዓሉን መቃረብ ይቀበሉታል፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ልክ እንደ ደመራ የሚነድድ በወረቀት የሚሰራ ቅርጽ ይበጅና በርካታ ህዝብ በተገኘበት እንዲቃጠል ይደረጋል። የፋሲካ በዓል ዕለት በሜክሲኮ ከቤተሰብ ጋር በመሆን እንዲሁም በአንድ አካባቢ እየተሰባሰቡ በጸጥታ የሚካሄድ ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ብቻ ነው የሚደረገው።
ጀርመኖች ኦስተርን ሲሉ የሚጠሩት የፋሲካ በዓል በሚያከብሩበት ዕለት በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ እንቁላሎች ለምግብነት ይቀርባሉ፡፡ በሀገሪቱ ስቅለተ አርብና የትንሳኤ ቀናት በዓል በሚል የታወጁ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ፋሲካ ረዘም ያለ አከባበር ያለው ነው፡፡ በስቅለተ አርብ እለት ከክርስትና ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው ብለው የሚያምኑትን የዓሳ ምግብ የሚመገቡት ጀርመኖች በዓሉን የሚያደምቁና ለልጆች ስጦታ የሚያድሉ ‘ኢስተርን በኒ’ ወይም የፋሲካ ጥንቸሎችም አንዱ የአከባበሩ ማድመቂያዎቻቸው ናቸው፡፡ ‘ፍሮህ ኦስተርን’ ወይም ለበዓለ ፋሲካ እንኳን አደረሰን የሚባባሉት ጀርመኖች ፋሲካን ጥንታዊና ኃይማኖታዊ በሆኑ ስርዓቶች ነው የሚያከብሩት፡፡
የፋሲካ በዓል በሩሲያ ውስጥ የዓመቱ ዋነኛ ኃይማኖታዊ በዓል ነው። ከፋሲካ በዓል በፊት ባለው ቀን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የምሽት አገልግሎቶችን በማካሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ኃይማኖታዊ ሰልፎችን ያዘጋጃሉ። ጠዋት ጎረቤቶችን ከመጎብኘት እና የትንሳኤ እንቁላሎችን ከመስጠት ይጀምራል። በዕለቱ የሚሰማው የተለመደው ሀረግ ታዲያ “ክርስቶስ ተነሥቷል!” ቀጥሎም “በእውነት ተነሥቷል!” የሚሉትን ሲሆን ይህን ተክትሎ በባህላዊ ሰላምታ በመተቃቀፍ ሰላምታ በመለዋወጥ በዓሉ ይከበራል፡፡
በሩሲያ የፋሲካ በዓል ሰባት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ቅዱስ ሳምንት ወይም ‘ሴድሚሳ’ ይባላል፡፡ በፋሲካ በዓል ግን የተትረፈረፈ ምግብ ቀን ነው፡፡ ከታላቁ ዐብይ ጾም በኋላ በጣም ጣፋጭ ምግቦች በጠረጴዛዎች ላይ ይገኛሉ። ከዋና ዋና ምግቦች መካከል የፋሲካ ኬኮች፣ ኩሊች (በዕለቱ የሚጋገር የዳቦ አይነት) እና ቀለም የተቀቡ እንቁላሎች ይገኙበታል፡፡ በሩሲያ ውስጥ በትንሳኤ በዓል ለተቸገሩ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና እንግዶች ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ሆስፒታሎች እና እስር ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች ስጦታዎችን መላክ የተለመደ ነው።

ፋሲካን ‘ፓኩዌስ’ ሲሉ የሚጠሩት ፈረንሳዊያን በዋናነት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አማኒያን በመሆናቸው ከጸሎተ ሐሙስ ጀምሮ የቤተክርስቲያን ደውሎች እንዳይደወሉ ያደርጋሉ፡፡ ፈረንሳዊያን ይህን የሚያደርጉት የክርስቶስን ስቃይና ሞት ለማሰብ ሲሆን ደውሎቹ ዳግም የሚደወሉት በትንሳኤ ዕለት ነው፡፡ ህጻናት በነዚህ ጊዜያት ደውሎቹ ሊቀ ጳጳሱን እንኳን አደረሰዎት ለማለት ወደ ሮማ ሄደዋል ተብለው በወላጆቻቸው ይነጋራቸዋል፡፡ በትንሳኤ ዕለት የደውሎቹ ድምጽ ዳግም ሲሰማ ሰዎች በየመንደሩ ተቃቅፈውና ተሳስመው እንኳን አደረሰህ እየተባባሉ የክርስቶስን መነሳት በደስታ ማክበራቸው በፈረንሳይ የተለመደ የአከባበር ስርዓት ነው፡፡
ክርስቶስ 40 ቀናት በጾም በጸሎት ማሳለፉን ለማሰብ በሰሞነ ህማማት ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ፈረንሳዊያን በጾም በጸሎት ነው የሚያሳልፉት፡፡ ማክሰኞ ዕለት በመላው ሀገሪቱ የህማማት መግቢያን በማስመልከት ታላቅ ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡ በዚህ ቀን በተለይ የሚዘጋጁ ድግሶችና ምግቦች በፈረንሳይ ለየት ያሉ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በፈረንሳይ ያለው የፋሲካ በዓል አከባበር ስርዓት ከሌሎች የምእራባዊያን ሀገራት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡
በስፔን የክርስቶስን መሰቀል በማሰብ ለንስሃ ወይም ከእግዚአብሄር ጋር ለመታረቅ በሰሞነ ህማማት የተለየ ልብስ
መልበስ የበዓሉ አንድ አካል ነው፡፡ በትንሳኤ ዕለት ደግሞ የንስሃ አባት ለንስሃ ልጆቻቸው የኬክ ስጦታ ያበረክታሉ። በትንሳኤ ጊዜ የእንቁላል ምግቦችም ይዘጋጃሉ፡፡ በወተት፣ በእንቁላልና በስኳር ርሶ በዘይት የተጠበሰ ዳቦም ይዘጋጃል። ይህ ዳቦ ደግሞ ከማር፣ ከስኳርና ከሌሎች ጣፋጮች ጋር ለገበታ የሚቀርብ ሲሆን፣ የወይን መጠጦችም በማባያነት ይዘጋጃሉ፡፡
በጣሊያን የፋሲካ በዓል አከባበር ስርዓት ከገና በዓል አከባበር በላይ በደማቁ የሚካሄድ ስነ ስርዓት ነው። በጣሊያን በፋሲካ ወቅት ሰዎች ከስራ በማረፍ ጭምር ነው በዓሉን የሚያከብሩት። በዚህ ሰሞን ጣሊያናዊያን ለሽርሽር ከከተማ ወጣ ማለታቸው የተለመደ ቢሆንም ከተሞቻቸውም ቢሆን በዓል በዓል በሚሸት ድባብ ውስጥ ነው የሚያሳልፉት፡፡ በንስሃ መንጻት አንዱ ኃይማኖታዊ ግዴታ ሲሆን በአቢያተ ክርስቲያናት የሚካሄደው ስነ ስርዓትም የጣሊያኖች የፋሲካ አከባበር አንድ አካል ነው፡፡ የኃይማኖት አባቶች በየቤተ ክርስቲያኑ ለሚመጡ ምዕመናን ቡራኬ ይሰጣሉ፡፡
በተለይ ሮም በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሚደረገው ቡራኬ ሰፊ እድምተኛ ያለውና ታላቅ የበዓሉ ስነ ስርዓት ነው፡፡ በስቅለት ዕለት ወይም በዕለተ አርብ በሮማ አደባባይ በመብራት ተምቦግቡጎ የሚደምቀው መስቀል በሊቀ ጳጳሱ የሚካሄደው ስነ ስርዓት መጀመርን የሚያመላክትና የኢየሱስ ክርስቶስን ለሰዎች ሲል መሰቀልን የሚገልጽ መሆኑ ይነገራል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ