የተማሪዎች የደንብ ልብስ አቅርቦት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲሟላ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የከተማ አስተዳደሩ የምገባ ኤጀንሲ የሩብ አመት የስራ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ሱፐርቪዥን አካሄዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሽታዬ መሃመድ፣ የሩብ አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

ኤጀንሲው በ21 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት 36 ሺህ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን እየመገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተማሪዎች ምገባም 810 ሺህ ተማሪዎችን በቀን 2 ጊዜ ቁርስ እና ምሳ እየመገበ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት አብራርተዋል።

የተማሪ የደንብ ልብስ እና መማሪያ ደብተር አቅርቦትን በተመለከተም የሸገር ከተማ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ጭምር ታሳቢ በማድረግ ለ1 ሚሊዮን 34 ሺህ ተማሪዎች አቅርቦቱ እየተፈጸመ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ኤጀንሲው የሰው ኃይል ድልድል ክፍተቶች እና የቢሮ እጥረት ያለበት በመሆኑ ምክር ቤቱ ለመፍትሄው ድጋፍ እንዲያደርግም ኤጀንሲው ጠይቋል።

የተማሪ የደንብ ልብስ በወቅቱ አለመድረሱ በኤጀንሲው ውስንነት የተነሳ ሲሆን ለመፍትሄው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ ሊኖር ይገባል ተብሏል።

የምክር ቤቱ የሴቶች እና ማህበራዊ ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘይነባ ሽኩር በሰጡት መመሪያ ፣ የተማሪዎች የደንብ ልብስ አቅርቦት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲሟላ አሳስበዋል።

ለዚህም የሚመለከታቸው ተቋማት ከምገባ ኤጀንሲው ጋር በመቀናጀት የተማሪ የደንብ ልብስ አቅርቦት በአጭር ጊዜ የሚፈጸምበትን አግባብ እንዲያሳኩ ጠይቀዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review