የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ ምን ጥቅም አስገኘ?

You are currently viewing የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ ምን ጥቅም አስገኘ?

ብድሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ገበያውን በማረጋጋት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል

የዋጋ ንረት የሚፈጥረውን የኑሮ ጫና ሚዛን ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ካላቸው ተቋማት መካከል የአምራች እና የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ይጠቀሳሉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነዋሪ ሕዝብ ላላቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የህብረት ሥራ ማህበራት ወሳኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ምክንያቱም፤ በየጊዜው የሚፈጠሩ የኢኮኖሚና መሰል ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ወይም መፍትሄ እየሰጡ ለመሄድ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው ለብቻ ከመቆም ይልቅ በጋራና በህብረት መንቀሳቀስ ስለሚገባ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ 11 የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች እና 154 መሠረታዊ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማህበራት በዋናነት ለህብረተሰቡ መሠረታዊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማቅረብ ኃላፊነትን የሚወጡ ናቸው፡፡ ማህበራቱ የሚያቀርቧቸው መሰረታዊ ምርቶች በነጋዴው ማህበረሰብ ከሚቀርበው መሰል ምርት በጥራት፣ በብዛትና በዋጋ ሲነፃፀሩ በሸማቹ የሚመረጡ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም የተቋቋሙት አባሎቻቸውንና ማህበረሰቡን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንጂ ለትርፍ ስላልሆነ ነው፡፡

የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች እና ማህበራቱ ከ2013 በጀት ዓመት በፊት በአገልግሎታቸው ብዙ ክፍተት የሚታይባቸው እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ አባሎቻቸው እና ሸማች ማህበረሰቡ የሚፈልገውን ምርትና አገልግሎት ከማህበራቱ ለማግኘት እጅግ ሲቸገር ቆይቷል፡፡ ለችግሩ በመነሻነት ከሚነሱ ጉድለቶች መካከል የማህበራቱ የሥራ ማስኬጃ የፋይናንስ እጥረት አንዱ ነበር፡፡ ይህንን ችግር በአግባቡ የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ2013 በጀት ዓመት አጋማሽ አካባቢ የወሰነው ታሪካዊ ውሳኔ፤ ማህበራቱ ከችግራቸው እንዲወጡ እና ለተጠቃሚው አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህም ውሳኔ በተመረጡ እና አስፈላጊ ለሆኑ ምርቶች መግዣ የሚሆን የ1 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ለማህበራቱ ፈቅዶ ወደ ሥራ ያስገባ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ያለማቋረጥ አገልግሎት ላይ የዋለው ይህ ከፍተኛ ገንዘብ ለማህበራቱ ያበረከተላቸውን አስተዋፅኦ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኙ 11 የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች መካከል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የምዕራብ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን አንዱ ነው፡፡ ዩኒየኑ በስሩ 19 መሰረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት እና ከ58 ሺህ በላይ አባላት አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 34 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

የምዕራብ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ቶሌራ፤ ስለ ዩኒየኑ አገልግሎት እና የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ስላበረከተው አስተዋፅኦ ማብራሪያ ሰጥተውናል። እሳቸው እንደገለፁት፤ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች አገልግሎታቸውን የሚሰጡት በአብዛኛው አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነው። አገልግሎቱን በዓይነት፣ በመጠን እና በጥራት ከፍ ለማድረግ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት እያንዳንዱ ዩኒየን የ100 ሚሊዮን ብር ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡ የምዕራብ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየንም ይህንን ገንዘብ በመጠቀም ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡ ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ እንደ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ… የመሳሰሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ከአምራቾች በብዛት በመግዛት ለተጠቃሚዎች በጥሩ ሁኔታ ማድረስ ተችሏል፡፡

የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ከተመቻቸ በኋላ የመጣውን ለውጥ ከቀድሞው ሁኔታ ጋር በማነፃፀር አቶ በላይ ቶሌራ እንዳብራሩት ከሆነ፤ ከ2013 በጀት ዓመት በፊት የምዕራብ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ዓመታዊ የምርት ግዢና ሽያጭ መጠን ከ100 ሚሊዮን ብር በታች ነበር፡፡ ለዩኒየኖች የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ በኋላ ዩኒየኑ ዓመታዊ የምርት ግዢና ሽያጭ መጠን ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል። በምርት ደረጃ ያለውን የግዢ መጠን ልዩነትን ለማሳየት የጤፍ ምርትን ብንመለከት ቀድሞ ከነበረው ከ500 እስከ 1 ሺህ ኩንታል የነበረውን፤ አሁን ላይ ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ ደርሷል፡፡ ውስን የነበረውን የምርት ግዢ መፈፀሚያ አካባቢ ማስፋት ተችሏል፡፡ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ከሚገኙ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ምርቶችን በዓይነት፣ በዋጋ፣ በጥራት፣ በብዛት አወዳድሮ የመግዛት አቅምን ፈጥሯል። ከዓመት ዓመት በዩኒየኖች እና በስራቸው ባሉ መሰረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት መጋዘኖች በቂ የምርት ክምችት እንዲያዝ አግዟል። የገበያ ዋጋው በአንፃራዊነት እንዲረጋጋ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ባይመቻች ኖሮ፤ ዩኒየኖች ከአባላት በሚሰበስቧቸው መዋጮዎች እና በሚያገኙት አነስተኛ ትርፍ አሁን ያለውን አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ማድረስ አይታሰብም ነበር፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ተክሌ በተመሳሳይ ዩኒየናቸው እና በስራቸው ያሉ 15 መሠረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት እንደከተማ አስተዳደር በተመቻቸው የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት አማካኝነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ማግኘታቸውን አልሸሸጉም፡፡ ካገኟቸው መሰረታዊ ጠቀሜታዎች መካከል የአገልግሎታቸውን ዓይነት በጥራትና በተደራሽነት ከፍ አድርጎላቸዋል። መሠረታዊ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛት እና በጥራት በመግዛት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲያደርስ አቅም ፈጥሯል።

“የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ በከተማዋ ያለውን የግብይት ዑደት በአንፃራዊነት እንዲረጋጋ ወሳኝ አስተዋፅኦ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ወቅታዊውን የጤፍ ዋጋ በምሳሌነት ብናነሳ፦ አንድ ኩንታል(100 ኪሎ ግራም) ነጭ ጤፍ ዋጋ ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር የገባ ሲሆን፤ ተመሳሳይ ምርት በኩንታል በ12 ሺህ ብር ዋጋ በእኛ ዩኒየን ስር ባሉ ሱቆች ለተጠቃሚዎች እየተሸጠ ይገኛል” ያሉት የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ፤ በነጋዴ እና በሸማች ማህበራት መካከል ያለው የተመሳሳይ ምርት ሰፊ የዋጋ ልዩነቱ ዋና ምክንያት፤ ከተማ አስተዳደሩ ያመቻቸውን የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት በመጠቀም ዩኒየኑ የግብርና ምርቶችን ወቅቱን የጠበቀ ግዢ በብዛት መፈፀም እና በቂ ክምችት መያዝ በመቻሉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ የማህበራቱ የምርት አቅርቦት ከፍተኛ እና በዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑ ደግሞ ነጋዴው ከዚህም በላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርግ የሚችልበትን ያልተገባ አካሄድ መስመር እንዲይዝ አድርጓል፡፡ የዋጋ ልዩነቱ በጤፍ ብቻ ሳይሆን፤ በተዘዋዋሪ ብድሩ ገንዘብ ግዢ እንዲፈፀምባቸው በተመረጡ ምርቶች ሁሉ ይታያል፡፡ በፓስታ ላይ በካርቶን ያለው የዋጋ ልዩነት ከ2 መቶ ብር በላይ ነው፡፡ መኮሮኒ የ400 እና የ500 ብር ልዩነት አለው። ዱቄት በማህበራት የሚቀርበው በገበያ ላይ ካለው የመሸጫ ዋጋ በኩንታል በትንሹ የ500 ብር ቅናሽ አለው፡፡

የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ የፈጠረው መልካም ሁኔታ፤ ማህበራቱ በአባልነት ላቀፏቸውና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መምህራን በመሆኑ መሠረታዊ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በረጅም ጊዜ ክፍያ እና በፍትሃዊነት ለዜጎች የማዳረስን ኃላፊነት እንዲወጡ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደር አምራች ዩኒየኖች፣ ከኢንዱስትሪዎች… የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች መግዛት መቻላቸው፤ በግብይት ስርዓቱ ውስጥ የሚገቡትንና ለዋጋ ጭማሪ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ የቆዩ ደላሎችን ከግብይት ሥርዓቱ ማስወጣቱንም በበጎነት አንስተዋል፡፡ የምርቶች አቅርቦት በዓይነትም በጥራትም እንዲጨምር፣ ፍትሃዊ ስርጭት እንዲኖር፣ የገበያ ዋጋ እንዲረጋጋ ለማገዝ ከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገውን የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ማስቀጠል እና ከፍ ማድረግ እንደሚኖርበት ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ከመመቻቸቱ በፊትና አሁን ላይ ያለውን አጠቃላይ ለውጥ በተመለከተ የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየንን ነባራዊ ሁኔታ በማሳያነት በማንሳት ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት፤ የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ከመመቻቸቱ በፊት የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ዓመታዊ የምርት ግዢና ሽያጭ(የግብይት) መጠን ከ28 እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነበር። ከ2013 በኋላ የግብይት ምጣኔው በየዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ብቻ ዩኒየኑ የ480 ሚሊዮን ብር ግብይት አከናውኗል፡፡

የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ከመመቻቸቱ በፊት ዩኒየኑ የነበረው ጠቅላላ ሃብት(ቋሚና ተንቀሳቃሽ) መጠን 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነበር። ከዚህ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ወይም በካሽ ያለው ሃብት መጠን ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ ነበር። በዚህ ገንዘብ ደግሞ የሸማቹን ማህበረሰብ ፍላጎት የሚያሟላ በቂ፣ ጥራት ያለው፣ በዋጋው የተመጣጠነ ምርት ማቅረብ አይቻልም ነበር። ምርቶችን በመጋዘን መያዝ አይታሰብም ነበር። የገባው ምርት ወዲያው ተሰራጭቶ ያልቃል። ከተማ አስተዳደሩ የብድር አቅርቦት ለማህበራቱ እንዲመቻች ማድረጉ ይህንን ጉድለት መቅረፍ አስችሏል፡፡ ይህንን መረጃ እየተለዋወጥን ባለንበት (ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም.) ላይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የንጋት በንፋስ ስልክ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት በመጋዘን በክምችት ይዟል፡፡ ከ2 ሺህ ኩንታል   በላይ ጤፍ፣ ከ500 ኩንታል በላይመኮሮኒ፣ ከ1 ሺህ ካርቶን በላይ ፓስታ በመጋዘኑ በክምችት ተይዟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፤ ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድልም ፈጥሯል። ዩኒየኑ ቀድሞ በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ በቋሚነት ቀጥሮ የሚያሠራቸው ዜጎች ቁጥር ስድስት ብቻ ነበር፡፡ አሁን ላይ አሥራ አራት ደርሷል። በጫኝና አውራጅ ሥራ ላይ ለተሰማሩ አሥራ ሁለት ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በተመሳሳይ በዩኒየኑ ስር ያሉ አሥራ አምስቱም መሰረታዊ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት አገልግሎታቸውን በማሳደጋቸው፣ አዳዲስ ስምንት ወፍጮ ቤቶች ለአገልግሎት በመብቃታቸው ከነባሩ ሠራተኛ በተጨማሪ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የአጋር አራዳ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን በከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመተግበር ላይ የሚገኘው የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት በስሩ ያሉትን አስር መሠረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ አባሎቻቸውንና በክፍለ ከተማው የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረጉን የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደለ ነግረውናል፡፡

“የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ከመመቻቸቱ በፊት የነበረው የዩኒየኑ የአገልግሎት ሁኔታ በጣም ውስንነት ያለበት ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህ ብዙ መሻሻሎች እና ለውጦች መጥተዋል፡፡ ለህብረተሰቡ የምናቀርበውን ምርት በዓይነት፣ በጥራት፣ በመጠን እና በዋጋ ተወዳዳሪና ተመራጭ ማድረግ ተችሏል። በተለይ መሰረታዊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወቅቱን የጠበቀ ግዢ በብዛት የመፈፀም አቅማችን አድጓል፡፡ በመጋዘን የምንይዘውና የምናሰራጨው የምርት መጠን እና ዓይነት ከፍ ብሏል” ያሉት የአጋር አራዳ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ፤  ዩኒየኑ በአንዴ ግዢ ብቻ እስከ 5 ሺህ ኩንታል ጤፍ ግዢ በመፈፀም እና በመጋዘን በማከማቸት በመሠረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የማሰራጨት አቅምን መፍጠሩን ጠቁመዋል። በዓመት በድምሩ ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ ለተጠቃሚዎች እያሰራጨ እንደሚገኝ በመጥቀስ ይህ ከሦስት ዓመት በፊት ይህ የማይታሰብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህንን መረጃ በተቀበልንበት ወቅት (በህዳር ወር 2017 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንት ላይ) የአጋር አራዳ የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦትን በመጠቀም ብዛት ያላቸውን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች አከማችቶ እያሰራጨ ይገኛል። ለአብነት ጤፍ ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ በመጋዘኖች ተይዞ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ የስንዴ ዱቄት በእያንዳንዱ የመሠረታዊ ሸማች ማህበራት ሱቆችና መጋዘኖች ውስጥ በበቂ ሁኔታ ይገኛል፡፡ በኪሎም ከ85 ብር ባልበለጠ ዋጋ በመሸጥ ላይ ነው፡፡ በቂ ክምችት ያለውን የመኮሮኒ ምርት በኪሎ ከ110 ብር ባልበለጠ ዋጋ በማህበራቱ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በዩኒየኑ ስር የሚገኙ መሠረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ጥራት ያለውን ጤፍ አስፈጭተው ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡት የአንድ ኪሎ ዋጋ 120 ብር ነው፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ለሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የፈቀደው የአንድ ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት ባለፉት ዓመታት ገበያውን የማረጋጋት ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን ያነሱት የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሃብተየስ ዲሮ፤ የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ለ11 የሸማቾች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች እኩል በማሰራጨት፤ የተመረጡ እና መሰረታዊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሃብተየስ ዲሮ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ እንደ አገር በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ እና የድርቅ ችግሮች የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ መጠን እንዲያሻቅብ አሉታዊ ጫና እንደነበራቸው ያነሱት ምክትል ኮሚሽነር ሃብተየስ፤ “ይህንን አስቸጋሪ ፈተና እንደከተማ አስተዳደር ተቋቁሞ ለማለፍ የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦቱ ቁልፍ አስተዋፅኦ አድርጓል። ለክፉ ጊዜ የደረሰ ባለውለታም ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የገበያው ዋጋ አሁን ባለበት ደረጃ ለመገኘት የብድር አቅርቦት ድርሻው ከፍ ያለ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ይህን ወሳኝ ውሳኔ አስተላልፎ መተግበር ባይችል ኖሮ፤ የማህበራቱ ሚና ትርጉም ያለው አይሆንም ነበር” ብለዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለው እንዳብራሩት፤ አሁን ላይ በ2016 በጀት ዓመት የተገዙና ከፍተኛ መጠን የግብርና ምርቶች በዩኒየኖች ተገዝተው በክምችትነት የተያዙ አሉ፡፡ እነዚህ ምርቶች ለተጠቃሚው በተመጣጠኝ ዋጋ እየተሰራጩም ነው። በዚህ ዓመትም ምርትን ገዝቶ ለማስገባት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በያዝነው የህዳር ወር ላይ የምርት ግብይት ለመፍጠር የሚያስችል ትልቅ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡ በመድረኩም ከፍተኛ አመራሮች፣ የሸማች ህብረት ሥራ ዩኒየን አመራሮች፣ በክልሎች የሚገኙ የአምራች አርሶ አደር ዩኒየን አመራሮች፣ የግል ኢንዱስትሪ አመራሮች የሚገኙ ይሆናል፡፡ ይህ መድረክ በ2017 በጀት ዓመት የሚከናወነውን የምርት ግብይት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የገበያ ትስስር ይፈጠርበታል። ከተማ አስተዳደሩ ይህንን በጀት የመደበው ለጉዳዩ ትኩረት እና ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ በአግባቡ በመምራት ለታለመለት ዓላማ ማዋል ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review