የተገፉ እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እድል ያጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እምባ ሲታበስ ማየት ደስታን ይሰጠናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
AMN-ሚያዚያ 09/2017 ዓ.ም
ዛሬ 446 ቤቶችን በመገንባት ለአቅመ ደካሞች፣ ለሀገር ባለዉለታዎች እና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ማስተላለፋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ከንቲባዋ መርሐግብሩን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ከተማ አስተዳደሩ ከከተማዋ ህዝብ በሚሰበስብው ገቢ ከሚያከናወናቸው ታላላቅ የልማት ስራዎች ጎን ለጎን በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶችን እና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሰዉ ተኮር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የተገፉ እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እድል ያጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እምባ ሲታበስ ማየት ደስታን ይሰጠናል ብለዋል ከንቲባዋ።

ዛሬ ለነዋሪዎች ከተላለፉ 446 ቤቶች ዉስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎላጎል አካባቢ የሚገኙትን ቤቶች ግንባታ ላከናወኑት ለገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ሌሎች በጎ ፈቃደኛ ባለሃብቶች እና ተቋማት ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
