
AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም
ዓለም ዓቀፉ የሜትሮሎጂ ድርጅት ትላንት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ከፍተኛ የሙቀት መጠን አስተናግዷል፡፡
በዓመቱ በአማካይ ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሼስ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን የሙቀት መጠን አንጻር ትልቁ ነው ተብሏል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ እጅግ ፈታኝ እና ትኩረት የሚሻ ወቅት ላይ እንደሚገኝ ያሳሰበው ድርጅቱ ያለፉት ዓሥር ዓመታት የተስተዋለው ሙቀት ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት ይልቅ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዓለም ዓቀፉ የሜትሮሎጂ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ሴሌስቶ ሳውሎ፣ የሙቀት መጠን መጨመር ዓለም ለተዛባ የአየር ንብረት እንድትጋለጥ ማድረጉን፣ ጥፋት ማስከተሉን እና ለበረዶ መቅለጥና ለባህር ውሀ መጠን መጨመር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2024 የተመዘገበውን ከፍተኛ መጠን ያለው የሙቀት መጠን በ2025 ቅድሚያ በመስጠት ለመሥራት አሁንም ጊዜ አለ ያሉት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ናቸው፡፡ ነገር ግን የመሪዎችን ተግባራዊ ምላሽ የሚሻ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የ2024ቱ የሙቀት መጠን የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ተጥሷል ለማለት አያስደፍርም ያሉት ጉቴሬዝ ስምምነቱ የአንድ አመት ብቻ ሳይሆን በዓሥር ዓመታት ውስጥ ያለውን የአየር ሁኔታ የሚገመግም ነው ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ የሙቀት መጠን በዓለማችን ዙሪያ የሚያሳድረውን ሁለንተናዊ ቀውስ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅ መገለጹን የዘገበው አናዶሉ ነው፡፡