የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በተለይም በዘርፉ የሚገኙ ተቋማት ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አስታወቁ።
ቢሮው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 14ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በአብርሆት የኪነ ጥበብ ማእድ መርሃ ግብር አካሂዷል።
መርሃ ግብሩን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሠው (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለመጠናቀቅ ጥቂት ምእራፍ የቀረው በመሆኑ ለግድቡ መጠናቀቅ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ግድቡ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያለው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ በዘርፉ ስር የሚገኙ ተቋማት ለግድቡ መጠናቀቅ የሚያከናውኑት ድጋፍ የላቀ ሊሆን እንደሚገባም የቢሮ ሃላፊዋ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጸ/ቤት ሃላፊ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ማድረጋቸወን ያስታወሱት ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ቀሪ የግድቡ ስራ እንዲጠናቀቅ የዜጎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማህበር እና ሌሎች የሴክተሩ አመራሮች በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ሲሆን ለግድቡ መጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።
በዝናሽ ሞዲ