AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
የቅድመ ኃይል ማመንጨት ሙከራ ስራው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖባቸው ወደ ዋና ስራቸው እንዲገቡ ዝግጁ ሆነው ከነበሩ ተርባይኖች መካከል ተርባይን ቁጥር 6 ሙሉ በሙሉ የሙከራ ስራው ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ስራ መጀመሩን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
400 ሜጋ ዋት ኃይል ከሚያመነጩት የታላቁ የህዳሴ ግድብ 11 ተርባይኖች መካከል ቁጥር ስድስት ተርባይን ወደ ኃይል ማምረት ስራ መግባቱን ያመለከተው ጽ/ቤቱ ተርባይኑ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሙሉ አቅሙ በላይ እስከ 401 ነጥብ 26 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተርባይን ቁጥር 5 የኮሚሽኒንግ ስራው የመጨረሻ ምዕራፍ ሙከራ ላይ ይገኛልም ብሏል፡፡
ሌሎቹ ዩኒቶችም እንዲሁ በተቀመጠላቸው እቅድ መሰረት ተራ በተራ ወደ ኃይል ምርት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
ተርባይን ቁጥር 8 እና ተርባይን ቁጥር 7 ሙሉ በሙሉ የሙከራ ሂደቱን አልፈው ተራ በተራ ወደ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት ሂደት መግባታቸውን ያመለከተው ጽ/ቤቱ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሳይቋረጥ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅሷል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ያመላተው ጽ/ቤቱ ዓመታዊ የኃይል ምርቱ ደግሞ 15ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ይሆናል መባሉን ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡