AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ ድጋፉን በቋሚነት አጠናክሮ መደገፍ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳሰቡ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት፣ የግድቡ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ የተጣለበትን 14ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ የንቅናቄ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ ግድቡ እየተጠናቀቀ መሆኑን አመላክተው፣ ኢትዮጵያዊያን ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቋሚነት መደገፍ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ምስክር ነጋሽ በበኩላቸው፣ ለግንባታው እስካሁን የወጣው ወጪ 240 ቢሊየን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገኘው 20.2 ቢሊየን ብር ያህል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ከሕብረተሰቡ እና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተደረገው ድጋፍም 5.8 ቢሊየን ብር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ የፕሮጀክቱ ተግባራት እስኪጠናቀቁ ድረስ ዛሬም እንደ ትላንቱ ህብረተሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት ዶ/ር ምስክር፣ ሌሎች ልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄው ከመጋቢት 01 እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድም ተመላክቷል፡፡
በሄለን ጀንበሬ