
በአዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ታላቁ የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ማህፀን እየፈለቀ ለም አፈርና ማዕድናትን እየጠራረገ እየወሰደ፤ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳይሰጥ መፍሰሱ የዘመናት ቁጭት ሆኖ ነበር የኖረው፡፡ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” እየተባለም ሲተረትበት ኖሯል፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ወረዳ የተበሰረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል። የኢትዮጵያ መንግስታት ተከታታይ የዓባይን ውሃ የመጠቀም ህልምና ፍላጎት በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ ወደ ተግባር የተሸጋገረበት፤ ቁጭት፣ እንጉርጉሮው ወደ ተስፋና ደስታ የተቀየረበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
እነሆ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል፡፡ አፈፃፀሙ 98 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል፡፡ ግድቡ አሁን ካለበት የመጠናቀቂያ ምዕራፍ ሲደርስ እንዲሁ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በግንባታው ሂደትና በዲፕሎማሲው የተለያዩ ውጣ ውረዶች አጋጥመው ታልፈዋል፡፡ ለስኬቱ ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያደረገው ተሳትፎና የመንግስት ቁርጠኝነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡
ለግድቡ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ካደረጉት መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያው አቶ ቸርነት ሻወል አንዱ ናቸው፡፡ “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ያደረገ፤ ሀገራዊ ስሜትን የቀሰቀሰ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሁላችንም ልብ ሲነሳ በቁጭት ሲንተከተክ የነበረው ሀሳብ ወደ ተግባር ሲገባ በጣም ተደስቻለሁ። በተለይ በእኔ ትውልድ ግድቡ እውን መሆኑ ኩራት ይሰማኛል። የዚህ አኩሪ ታሪክ ተካፋይ በመሆኔ እድለኛ ነኝ” ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ያነሳሉ፡፡

የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የኮሌጅ ተማሪ እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ቸርነት፣ በወቅቱ ለተለያዩ ወጪዎች ከሚሰጣቸው ገንዘብ በመቀነስ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የመንግስት ስራ ላይ ከተሰማሩም በኋላ ሁለት ጊዜ በደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ተሳትፈዋል፡፡ “አሁን ላይ ግድቡ ለፍፃሜ በመድረሱ ደስ ብሎኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተባበረ ምን ማድረግ እንደሚችል የህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው፡፡” ሲሉ ይህንን እንደምሳሌ በመውሰድ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ለመሆን መረባረብ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡
ሌላኛዋ አስተያየቷን ያጋራችን በክፍለ ከተማው በመልዕክተኝነት የምትሰራው ወይዘሪት መሰረት እስራኤል ከደመወዟ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት አስተዋፅኦ ማድረጓን ትናገራለች፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን የኩራት ምንጫችን ሆኗል፡፡ የግድቡን መጠናቀቅ በተስፋ ስንናፍቀው ነበር፤ አሁን ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በሀገራችን ያለውን ችግር በመቅረፍ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣልን አምናለሁ ስትል የተሰማትን ስሜት አጋርታናለች፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ዳንኤል ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ሀሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ እቅድ በማውጣት፣ ግንባታውን በውስጥ አቅም ለማከናወን የተወሰደው እርምጃ የህዝብና መንግስት ቁርጠኝነት የታየበት ነው፡፡ መንግስት ፕሮጀክቱን ለመገንባት ጥሪ ሲያቀርብ፤ ኢትዮጵያ የወንዙ አመንጪ ሀገር ሆና በወንዙ መጠቀም ባለመቻሏ ሲቆጭና ሲቆዝም የነበረው ህዝብ በአንድነት እና በእኔነት ስሜት ድጋፍ እንዲያደርግ አነሳስቷል፡፡
ህዝቡ ለግድቡ ሲያደርግ የቆየውና እየተደረገ የሚገኘው ድጋፍ በተለያየ መልኩ የሚገለፅ ነው፡፡
ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመስጠት፣ በሞራል፣ በጉልበት፣ አርሶ አደሩ የቤት እንስሳትን፣ እህልና የተለያየ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ዳያስፖራው፣ ሀብታምና ድሃ፣ ሴትና ወንድ፣ ህፃንና አዋቂ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት ልዩነት ሳይኖር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ የታየበት የአዲስ አበባ ድጋፍ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደ ሀገር እየተደረገ ባለው ድጋፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ግድቡ በሀገራዊ አቅም እየተገነባ ያለ እንደመሆኑ፣ ለግንባታው የአዲስ አበባ ህዝብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መጠነ ሰፊ ድጋፍ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሐምሌ 2003 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተደረገው ድጋፍ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚበልጥ አልነበረም።
ግንባታው ከተጀመረበት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ የኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚያመነጭ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በፕሮጀክቱ አመራር እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ሰፊ መሰናክሎች በማጋጠሙ የታቀደው ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ፕሮጀክቱ ላይ ያሉ ችግሮች ተገምግመው የብረታ ብረትና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ዓለም አቀፍ ልምድ ባላቸው ኩባንያዎች እንዲሰራና አመራሩ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ግድቡ ካጋጠመው ችግር እንዲላቀቅ ተደርጓል። በዚህም በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ፈጣን ለውጥና እድገት ታይቷል፡፡ በስራው መጓተት የተነሳ ተቀዛቅዞ የነበረው የህዝብ ድጋፍም በተሻለ ሁኔታ መነቃቃት ማሳየቱን ምስክር (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ከወትሮ በተለየ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ ከ2013 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና አመራራቸው ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረትና ክትትል ከፍተኛ ሚና እንደነበረውም አስረድተዋል፡፡
ምስክር (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ባለፉት 14 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ አብዛኛውም በቦንድ ግዥ እና የተወሰነው በልገሳ የተከናወነ ነው። ይህም ከዝቅተኛ ገቢ እስከ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ድምር ውጤት ነው፡፡
የግድቡ ግንባታ መፋጠንና እውን እየሆነ መምጣትን ተከትሎ የህዝብ አመኔታና ድጋፍ መጨመሩን አቶ ሰለሞንም ይጋሩታል፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባለው መረጃ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል። ይህም ህዝቡ እስከ መጨረሻው የሚያደርገው ድጋፍ መቀጠሉን ያሳያል። ባለፉት 14 ዓመታት እንደ ሀገር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከማህበረሰቡ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ይህም “ህዝብ ከወሰነ የትኛውንም ማድረግ እንደሚችል እኛ ያየንበት፤ ዓለምም የመሰከረበት ጉዳይ ነው” ይላሉ አቶ ሰለሞን፡፡
በአዲስ አበባ ከተማም በ2017 በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 506 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዓመቱ ከታቀደው በላይ ከ608 ሚሊዮን ብር በላይ (በአብዛኛው በቦንድ ግዥ እና በተወሰነ መልኩ በልገሳ) መሰብሰብ መቻሉን ምስክር (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግስት ሰራተኛውና አመራሩ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ በዓይነት ሁለት ባለሦስት መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት ድጋፍ አድርጓል። እንዲሁም አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና፣ የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሙዚየም መገንቢያ ከ15 ነጥብ 2 ሄክታር በላይ መሬት በማዘጋጀት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ በዲፕሎማሲው ረገድ ያጋጠሙ ጫናዎችን በመመከት ህብረተሰቡ ያደረገው ተሳትፎ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግድቡ ላይ ያሉ ችግሮች ተፈትተው የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ ሲመጣና የውሃ ሙሊት ሲከናወን ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራትና ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎች በርትተው እንደነበር በፕሮጀክቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚው አቶ ሰለሞን ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በድህነት ተዘፍቃ እንድትኖርና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና እንዳትወጣ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ከተከፈተው አሉታዊ ዘመቻ ባሻገር፣ ፕሮጀክቱን የሰላምና የደህንነት ጉዳይ አድርጎ በማየት እስከ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ በመወሰድ በተደጋጋሚ አጀንዳ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በወቅቱም ከሀገር ውስጥ ባሻገር የዳያስፖራው ማህበረሰብ፤ “ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ 86 በመቶ ውሃ የምታመነጭ ሀገር መሆኗን፣ አሁንም በርካታ ህዝቧ በጨለማ ውስጥ መብራት እና የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ሳያገኝ እንደሚኖር፣ የግድቡ ግንባታ የልማት ጉዳይ እንደሆነ እውነታውን በማሳወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል” ይላሉ አቶ ሰለሞን፡፡
በጹሑፍ፣ በጥናትና ምርምር፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ የኢትዮጵያ እውነታ በዓለም እንዲታወቅ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሀገር ውስጥም መገናኛ ብዙሃን፣ የምርምር ተቋማት፣ ግለሰቦች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መንገዶች ሀሳባቸውን ሲያካፍሉ ቆይተዋል፡፡ ግድቡ በደለል እንዳይሞላና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆንም በወንዙ ተፋሰስ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችም ችግኝ በመትከል ሲያደርጉ የነበረው ተሳትፎ ሌላው የህዝብ ተሳትፎ ማሳያ እንደሆነ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰሱ ሀገራትም የዓባይ (ናይል) ውሃ በፍትሐዊነትና ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችለው የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ህግ ሆኖ ወደ ስራ እንዲገባና የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንም እንዲቋቋም በር መክፈቱን አቶ ሰለሞን ያነሳሉ፡፡
ምስክር (ዶር) እንዲሁ፤ ግድቡ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማመንጨት የተሻገረ ዓላማ ያለው እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የመቆሟና ራሶን የመቻሏ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የተሳሳቱ የቅኝ ግዛት ውሎችን የሻረ ዳግማዊ ዓድዋ ነው፡፡ መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ሀብታምና ደሃ ሳይል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ያለምንም ልዩነት በአንድ ልብ ሀሳብ በአንድነት ለዘመናት ሲናፈቅ የነበረው በዓባይ ውሃ የመጠቀም መብት የተሳካበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአራት ወራት በፊት ግድቡን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ “በድህነታችን የተሳለቁብን፣ ካላችሁበት አረንቋ አትወጡም፤ የብልፅግናን ሽታ አታዩትም፤ መልማት አይቻላችሁም፤ መሻገር አይሆንላችሁም… ላሉን ግለሰቦችና ቡድኖች ህዝብና ሀገር ከወሰነ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ህዳሴም አረንጓዴ አሻራም ያሳያል” ነው ያሉት፡፡
በጥቅሉ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ራስ የመቻል፣ በራሳችን ፕሮጀክት ቀርፀን፣ አቅደን፣ መርተን፣ በራሳችን የፋይናንስ አቅም በመተባበር መስራት እንደቻልን ያሳየንበት ዳግማዊ ዓድዋ ነው። በቀጣይ ለመልማት ያለን ፍላጎትና አቅም የታየበት፤ የመንግስትና ህዝብ ቁርጠኝነት የታየበት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅም ቦንድ በመግዛት፣ በስጦታ እና በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያነጋገርናቸው ኃላፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ