ይቅርታ የሰው ልጅ አብሮ የመኖር ምሰሶ ነው፡፡ ይቅርታ በህብረተሰቡ ውስጥ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ አንዱን ከአንዱ እያስተሳሰረ ይኖራል። የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉትም ይቅርታ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብት ግሩም ጥበብ ነው፡፡ ግጭትና ብጥብጥ ባለበት ዓለም፣ ይቅርታ የተስፋ መስታወት ሆኖ የቆመ፣ የእርቅና የሰላም መንገዶችን የሚያደምቅ ብርሃን ነው ይላሉ ምሁራኑ፡፡
ዓለማችን ከመዘገበቻቸው አያሌ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ በይቅርታ የተፃፉ ታሪኮች ያላቸው ስፍራ የጎላ ነው። በፈላስፎች፣ የኃይማኖት መሪዎች እና የሥነ ምግባር ምሁራን ዘንድ የተከበረ ነው። እስከ ክርስቶት የተራራው ስብከት ከቡድሃ እምነት አስተምህሮ፤ ከጋንዲ እስከ ማንዴላ ጥበብ ድረስ መልዕክቱ ግልፅ ሲሆን፣ ይቅር መባባል የድክመት ምልክት ሳይሆን የሰውን መንፈስ ጥንካሬ የሚያሳይ እንደሆነ የደች ካቶሊክ ቄስ፣ ፕሮፌሰር፣ ጸሐፊ እና የኃይማኖት ምሁሩ ኑዌን ሄንሪ ጄም “የባካኙ ልጅ መመለስ” (The Return of the Prodigal Son: A Story of Homecoming) በተሰኘ መፅሐፍ ላይ አስፍረውታል፡፡
ታዋቂው የስነ መለኮት ምሁር ቦንሆፈር ዲትሪች “የደቀ መዝሙርነት ዋጋ” በተሰኘ ዳጎስ ያለ መፅሐፋቸው እንደጠቀሱት በዘመናችን፣ ይቅር ባይነት ብዙውን ጊዜ በቁጭት፣ በቁጣ፣ እና የበቀል ጥማት የተሞላ ይመስላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በራሳችን ማህበረሰቦች ውስጥ ግጭቶች መበራከታቸው ለዚህ አሳዛኝ እውነታ ምስክር ነው፡፡ በሀገራት መካከል ካለው መራራ ጠብ እስከ የቤተሰብ መቃቃር ድረስ የህብረተሰቡን መዋቅር የሚያናጋ፣ ይቅር አለማለት፣ ማለቂያ የሌለውን የስቃይና የመከራ አዙሪት እንዲቀጥል ያደርጋል በማለት የይቅርታን ዋጋ ገልፀውታል።
እንደ ኑዌን ሄንሪ ጄም ገለፃ ደግሞ ይቅርታ ድፍረትን፣ ትህትናንና መተሳሰብን የሚሻ የለውጥ ሂደት ነው። ይቅርታ ለጋራ ሰብዓዊነታችን እውቅና በመስጠት እና ሁላችንም ለስህተት የተጋለጥን መሆናችንን በመገንዘብ ለአብሮነታችን መጎልበት ከልባችን የምንቆርሰው ውድ ስጦታ ነው፡፡ በመሆኑም ይቅር ማለት የእያንዳንዱን ግለሰብ ተፈጥሯዊ ክብር እውቅና መስጠት ነው፡፡
ሆኖም ይቅርታ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም። የራሳችንን ስቃይ እና መከራ እንድንጋፈጥ፣ የክህደት እና የፍትህ እጦት ስሜቶችን እንድንታገል እና በውስጣችን ያለውን ጨለማ አሸንፈን እንድንወጣ ይጠይቀናል። ትዕግስትን፣ ጽናትን እና ተጋላጭነትን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። ቁስልን ወደ ፈውስ፣ ቂምን ወደ ርህራሄ የሚቀይር ፈዋሽ መድሐኒት ነው ይላሉ ኑዌን ሄንሪ ጄም።
ይቅርታ የብቸኝነት ተግባር ሳይሆን የጋራ ጥረት፣ ወደ ፈውስ እና ወደ ሙሉነት የሚደረግ የጋራ ጉዞ ነው። በውይይት እና በዕርቅ ውስጥ እንድንሳተፍ፣ ከልብ ማዳመጥ እና በታማኝነት እና በቅንነት መናገርን ይጠይቃል። የዘር፣ የኃይማኖት እና የአስተሳሰብ አጥር ተሻግረን የመተማመን እና የመግባባት ትስስር የምንፈጥረው ይቅርታ በምንለው ሰረገላ ፍቅር በምንለው የጋራ ጉዞ ነው ሲሉም ያክላሉ።
ለመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከትንሳኤ ምን ትምህርት መውሰድ አለበት? ከይቅርታ ጋር ያለው አንድምታስ ምን ይመስላል? የሚል ነጥብ በዚህ ፅሑፍ እናብራራለን፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቤላ ፈለገ ሰላም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባ ታመነ ኃይሉ፣ የሰው ልጅ በትንሳኤው ብርሃን የጨለማ ዘመኑ ተገፈፈ፤ በደሉ በይቅርታ ተሻረ፡፡ እናም ከትንሳኤው አስተምህሮ፣ ለነፍሳችን ብቻ ሳይሆን ለስጋችንም ረፍትን የሚሰጡ፣ መልካሙን መንገድ የሚመሩ እና ኑሯችንን የሚያጣፍጡ ብዙ ምስጢሮችን እንማራለን ይላሉ፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያው አቶ ማህደር ሳልህ በበኩላቸው፣ ኃይማኖታዊ ጥልቅ ትርጓሜው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ትንሳኤ የሚለው ቃል በራሱ ተሻግረው የማይጨርሱት ምዕራፍ አንብበው የማያገባድዱት መፅሐፍ ነው፡፡ ሞትን ድል ማድረግን፣ አለመኖርን በመኖር መተካትን ከዚህም ተሻግሮ በትንሳኤያችን ብርሃን የሌሎችን ጨለማ መግፈፍን፣ የሌሎችን መከራ መቀበልን፣ በደልን ይቅር ማለትን፣ ከምንም በላይ ፍቅርን ማስቀደምን ይህን ስናደርግ ደግሞ ሞትን አሸንፈን ከፍ ከፍ ማለትን የመሰለ ግሩም አስተምህሮ ያለው ድንቅ ቃል ነው ትንሳኤ ብለዋል፡፡
በተለይም ተበድሎ ይቅር ማለትን፣ ሁሉን ማድረግ እየቻሉ እራስን ዝቅ አድርጎ ለፍቅር መገዛትን እና ለሞት የሚያደርስ በደል እንኳን እየፈፀሙብን በፍፁም ትህትና ምህረትን ያገኙ ዘንድ ለበዳዮቻችን መመኘትን የመሳሰሉ ለምድራዊ ኑሯችን ስንቅ የሚሆኑ አስተምህሮዎችን ከትንሳኤው እናገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡
የቤላ ፈለገ ሰላም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባ ታመነ በበኩላቸው የክርስቶስ ፍፁም ፍቅር የተገለፀው በመስቀሉ ላይ በተከናወነ የቤዛነት ስራ ነው ይላሉ፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፣ “በዮሐንስ ወንጌል 15÷13 እንዲህ ተብሎ ተፅፏል፤ ‘ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም’። ይህም ብቻ ሳይሆን የክርስቶስ ፍፁም ፍቅር ጥንት በነብያት አስቀድሞ የተነገረለት ነው፡፡”
የድርሳነ ፈያታዊ ዘየማን መጽሐፍ አዘጋጅ መላከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሰናይ ምስክር ቅዱሳት መፃሕፍትን ዋቢ አድርገው እንደገለፁት ንጉስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ድምፁን ባሰማ ጊዜ የረቂቅ መለኮትን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ፍጥረቶች ሁሉ ወደቁ፡፡ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ተቀደደ፤ የቀኑ ብርሃን ጨለማ ሆነ፤ ሞት ደነገጠ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ ሙታንም ተነሱ፡፡
ፈያታዊ ዘየማንም እንዲህ አለ። “መልአክ ሆይ ቃሌን ስማኝ እነሆ ሰማያዊ ንጉስ ጌታህ ሕይወትን የሰጠኝ እርሱ ነው… ወደ ሕይወት ሀገር እገባ ዘንድ የይቅርታውን በር ከፈተልኝ፡፡ ከወደኩበት የጌታ ምህረት አነሳችኝ፡፡ ማለቱን መላከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሰናይ ምስክር ይናገራሉ፡፡ አዎ! ነገረ ትንሳኤው ለሰው ልጆች ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ መተሳሰብን አብሮነትን፣ ትህትናን የሚያስተምረን ነው፡፡ በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ከትንሳኤው ምስጢር ይህንን ሊማር እንደሚገባውም ጠቅሰዋል፡፡
አባ ታመነ እንደሚሉት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ጥላቻና መጠፋፋትን ያስወገደ፣ ሰላምን ያሰፈነ፣ እርቅን ያረጋገጠ ነው፡፡ ትንሳኤው በምድራዊው ሕይወታችንም ሆነ በሰማያዊ ሕይወታችን የላቀ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ክርስቲያኖች በምድራዊው ሕይወታችን በበጎ ስራ አሸብርቀን፣ ከሀጢያት እርቀን፣ በፍቅርና በአንድነት፣ በእርቅና በሰላም እንኖር ዘንድ ትንሳኤው ለስጋችን ብርታት ለመንፈሳችን ፅናት ይሆነናል፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከሞት በኋላ ትንሳኤ ሕይወት መኖሩን በሩቅ አይተን በተስፋ እንድንኖር ጉልበት ይሆነናል፡፡ በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ከትንሳኤው ትርጉም ለምድራዊ ኑሮው መልካም ስብዕናን ለዘላለማዊ ሕይወቱ ደግሞ የማያልቅ ስንቅን እንዴት መቅሰም እንዳለበት ሊማር እንደሚገባውም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያው ማህደር ሳልህ በበኩላቸው፣ የሰው ልጅ ማህበራዊ ኑሮውን የሚያጣፍጡ ቅመሞችን አንድም ከራሱ፣ አንድም ከተፈጥሮ ከፍ ሲልም ከኃይማኖታዊ ጥልቅ እና ረቂቅ አስተምህሮዎች ማግኘት ይችላል፡፡ በተለይም በየትኛውም ኃይማኖት ያሉ ትምህርቶች ሰውን በመልካም ስብዕና ከመቅረፅ አንፃር ድርሻቸው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ፍቅርና ይቅርታን ከማስተማር አንፃር ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ትንሳኤ ጥላቻን በፍቅር፤ አለመግባባትን በሰላም፣ ተስፋ መቁረጥን በፅናት፣ ቂም በቀልን በይቅርታ፤ ሀዘንን በደስታ ማሸነፍ እንደሚቻል ይማሩበታል፡፡ በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ እንደ ግለሰብም እንደ ማህበረሰብም ከፍ ሲልም እንደ ሀገር እያጋጠሙት ያሉ ፈተናዎችን በፍቅር እና በይቅርታ በማሸነፍ የሀገሩን ትንሳኤ ሊያበስር ይገባዋል ብለዋል፡፡
ወጣት ነፃነት ጉደታ በበኩሏ በትንሳኤው ውስጥ ለነፍሳችን ብቻ ሳይሆን በስጋዊ ኑሯችን የዋጠንን ጨለማ የሚያጠፋ ብርሃን አለ፡፡ ይሄውም በግለኝነት፣ በዘረኝነት፣ በክፋት፣ በበቀል እና በጥላቻ የጨለመውን ሕይወት በፍቅር፣ በሰላም፣ በምህረት፣ በእርቅ እና በመደማመጥ ፈትተን በመተሳሰብና በአንድነት እንኖር ዘንድ ከትንሳኤው ብዙ የምንማረው ቁም ነገር አለ ብላለች፡፡
የባይሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ እና የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሔኖክ ፍቃዱ፣ ትንሳኤ ይቅር ባይነትና የትህትና ተምሳሌት መሆኑን ጠቁመው፣ ትውልዱ ከዚህ በእጅጉ ሊማር ይገባዋል ብለዋል፡፡ “በእርግጥ አስተዳደጋችንም በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ነው” ያሉት አቶ ሔኖክ፣ “ትህትና እና ሰውን ማክበር አብሮን ያደገ መልካም ባህሪ ነው፤ ተላላቆችን ማክበር፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ መንገድ ማሻገር፣ ትራንስፖርት ላይ ሁሉ ሳይቀር ወንበር በመልቀቅ ታላቅን ማስቀመጥ ነው ባህላችን፡፡ ይህን በማድረግ የሚገኝ ውስጣዊ እርካታና ደስታ አለ፡፡ ስለዚህ ትውልዱ በዚህ መልክ የተቃኘ አመለካከት ቢኖረው ለሁሉም ወገን መልካም ይሆናል” የሚል ምክር ሰንዝረዋል፡፡
ክርስቶስ ትህትናና ይቅር ባይነትን አስተምሮናል፤ እኛም በማህበራችን አማካኝነትም ሆነ በግል ህይወታችን ይህን አርአያ ለመከተል እንሞክራለን ያሉት አቶ ሔኖክ፣ የተቸገሩ ወገኖችን አቅማችን በፈቀደ መጠን እናግዛለን፡፡ በዚህ ረገድ ወጣቶች በጣም ተባባሪ ናቸው፡፡ ይህ መልካም ተግባር ለወደፊቱ ትውልድም የሚሸጋገር መሆን አለበት፡፡ መልካምነት ገንዘብ በመስጠት ብቻ አይወሰንም፣ አቅመ ደካሞችን እግር ማጠብ፣ ገላቸውን እንዲታጠቡ ማገዝ፣ ፍቅርና እንክብካቤ መስጠት ዋጋ ያላቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡
ባይሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት ማህበር ከተመሠረተ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል። ለህፃናት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላትን ታሳቢ አድርጎ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ በሂደት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ አረጋዊያንን ወደ ማገዝም ተሸጋገረ፡፡ አሁን ከ100 በላይ ለችግሮች የተጋለጡ አረጋዊያንን እና ከ250 በላይ ህፃናት ተማሪዎችን በየቤታቸው ይደግፋል፡፡ ድጋፉ ወርሃዊ አስቤዛ ማሟላት፣ በዓላትን ደስታ ሳይለያቸው እንዲያሳልፉ ማድረግ፣ ቤታቸውን ማደስ፣ የተጠፋፉትን ማገናኘት፣ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ጎዳና ላይ ያሉ ወደ ማዕከላት እንዲገቡ ማስቻልን ያጠቃልላል፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተ ክርስቲያን ሪቨረንድ ተዘራ ያሬድ ˝በትንሳኤው ምን አገኘን˝ በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ፅሑፋቸው እንደገለፁት በትንሳኤ፣ ዳግመኛ ውልደትን፣ ሕያው ተስፋን፣ ፅድቅን እና አለመጥፋት አግኝተናል፡፡
ፀሐይ ወጥታ እንደምትጠልቅ የሰው ልጅም እንዲሁ በምድር ላይ ታይቶ ይጠፋል፡፡ ፀሐይ ዳግም ብርሃኗን ተጎናፅፋ እንደምትወጣ የሰው ልጅም እንዱሁ ይነሳል፤ ይላሉ የክርስትና ኃይማኖት ምሁራን፡፡ ዋናው ነገር ከትንሳኤው ትምህርት ወስደን ለስጋም ለነፍስም ስንቅ ይሆነን ዘንድ መልካምነትን፣ ፍቅር እና ይቅርታን በልባችን አንግሰናል ወይ? የሚለው ነው፡፡
በመለሰ ተሰጋ