የትውልዱ ፕሮጀክቶች

You are currently viewing የትውልዱ ፕሮጀክቶች

 በኮሪደር ልማቱ የደቀቁ ሰፈሮችና አካባቢዎች በተሻለ መልኩ እየተቀየሩ ነው

                                                                                    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት መግቢያ በር፣ የሀገር ገፅታ መስታወት ናት።  የሁሉም መድመቂያና ተናፋቂ ማዕከል ስለመሆኗም ብዙዎች ይመሰክሩላታል። አዲስ አበባ በየዘመናቱ አዲስ እና አበባ እየሆነች ለተለያዩ ከተሞችም ልምዷን እና ስልጣኔዋን እያጋራች ስለመቀጠሏ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

በተለይ በቅርቡ ከተማዋን ከስልጡን የዓለማችን ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ እየተሰሩ ባሉ የኮሪደር ልማቶች አዲስ አበባ በትክክልም አዲስም፤ አበባም እየሆነች መምጣቷን በቅርቡ የተከናወኑ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ታላላቅ ጉባኤዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩልም ከቦሌ እስከ መገናኛ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ፣ ከፒያሳም በቸርችር ጎዳና ወደ ሜክሲኮ ቢያሻን በመኪና አሊያም በእግር ዘወር ዘወር ብንል ልማቱ ራሱ ይናገራል፡፡ “አዲስ አበባማ፡ አዲስ አበባማ፣ ሽር ነው በጫማ” እንዳለው ዘፋኙ፡፡

የዝግጅት ክፍላችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አሮጌ መልኳን እንደ ንስር አድሳ፣ አዲስ ግርማና ሞገስን ተላብሳለች፡፡ አዲስም፣ አበባም ሆናለች፡፡ እነ እሪ በከንቱ፣ እነ ካዛንቺስ፣ እነ ዶሮ ማነቂያ፣ እነ ተረት ሰፈርን የመሳሰሉ አካባቢዎች የትላንት ጎስቋላ መልካቸው እንደ ደመና ተገፍፎ አዲስ ድምቀትን እየተላበሱ ነው፡፡

እነዚያ ጭንቅንቅ ያሉ መንገዶች፣ ጣሪያቸው ያረጀ፣ ማገራቸው የላላ፣ ምሶሷቸው ያዘመመ እና ባለ ላስቲክ ግድግዳዎቹ የደቀቁ ስፍራዎች በውብ መናፈሻዎች፣ በሰፋፊ መንገዶች እና በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እየተተኩ ነው። በርግጥም አዲስ አበባ ገና ከጫጉላ ቤት እንደወጡ ሙሽሮች፣ እንደ ቀይ ሐር ፈትል፣ በለምለም መስክ ላይ እንደሚቦርቁ እንቦሶች እና እንደ ተከፈለ ሮማን ዐይንንም ልብንም እየማረከች ነው፡፡

ታዲያ በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ያለችው አዲስ አበባ፣ ብቻዋን መዘመንን የፈለገች አይመስልም፡፡ ዘመኑን የዋጀውና ትውልድን ታሳቢ ያደረገው ለውጧ ወደ ሌሎቹም ከተሞችም እንዲስፋፋ ልምዷን በማካፈል ላይ ናት፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የቢሾፍቱና የጎንደርን የኮሪደር ልማት ስራዎችን እንዲሁም ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮችም በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ከተሞችን የኮሪደር ልማት ስራዎችን እያስተባበሩ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የኢትዮጵያ ከተሞች እና አካባቢዎች ርቀት በኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ መሐል ፒያሳ (00 ኪሎ ሜትር) እንደሚጀምር ሁሉ የከተሞችን ጎስቋላ እና የደቀቀ ማንነት ቀይሮ እንደ አዲስ የውበት ሸማን የሚያጎናፅፈው የኮሪደር ልማትም ከፒያሳ ጀምሮ ወደ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች በመስፋፋት በስኬት ላይ ስኬትን እያስመዘገበ ነው፡፡ ይህም ለሁሉም ከተሞች መስራት እንደሚቻል ያሳየና በውጤትም የተለካ ነው ይላሉ የከተማ ልማት ባለሙያዎች፡፡

የከተማ ልማት ባለሙያና የግል አማካሪ ኢንጅኒየር ታደሰ ተቋመ እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች በመስፋፋት አስደናቂ የከተሞች ለውጥን እያሳየ ያለው የኮሪደር ልማት በከተሞች መካከል የትብብር መንፈስን ያበረታታል፤ ለተሻለ የኑሮ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ለዘላቂ እምርታ ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ እንዲህ አይነት ልማት በተለይም አሁን ያለው ብቻ ሳይሆን መጭው ትውልድ በተጎሳቆለ አካባቢና ሁኔታ ውስጥ ሕይወቱን በአስቸጋሪ መልክ እንዳይገፋና ደስተኛ ሆኖ የሀገሩን ከፍታ እንዲያስቀጥል ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡

አክለውም ከተማዋ ልምዷን ለሌሎች ከተሞች እያካፈለች ያለበት ሂደትና በጎንደር፣ በጅማ፣ በባሕር ዳር፣ በሐረር፣ በሐዋሳ እና መሰል ከተሞች እየመጣ ያለው ለውጥ ሲታይ አዲስ አበባ በከተማ ልማት ገጽታም መሪ ኮከብ ሆና መውጣቷን የሚመሰክር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ ምንትዋብ አስረስ፣ “ከተማዋ በርግጥም ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ምቹ ሆና እየተሰራች ነው፡፡ አሁን ልጆቻችንን ወስደን የምናጫውትበት ቦታ አይቸግረንም፤ በየጎዳናዎቹ መናፈሻ ስፍራዎች እና ፏፏቴዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የልጆች መጫወቻዎች አሉ፡፡ እየተሰሩ ያሉ ልማቶችም ፅዱ በመሆናቸው ጤናችንን እየጠበቅን የተሻለ ሕይወትን ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንመራ ያስችላሉ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ከተማ ልማት ባለሙያው ኢንጅኒየር ታደሰ ገለፃ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ለሁሉም ከተሞች መስራት እንደሚቻል ያሳየ ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከተማ ከማሳመር በዘለለ ብዙ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል። በተለይም ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ የልማት ስራን በአጭር ጊዜ፣ በጥራት እና በህብረት መስራት እንደሚቻል ያሳየም  ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሐሙስ የመንግስትን የ8 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት የኮሪደር ዋና እሳቤው መልካም ሀገር እና ከተማን ጥሎ መሄድ ነው፡፡ ልጆቻችን ሌላ ናፋቂ ሳይሆኑ በሀገራቸው የተሻለ ከባቢ ውስጥ እንዲኖሩ ማስቻል ነው፡፡ የደቀቁ ሰፈሮችና ለማየት የሚያስቸግሩ አካባቢዎች በተሻለ መልኩ እየተቀየሩ ነው፡፡ ይህ ለውጥ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባም ውጭ ይህንን መሰል ልማት በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት በሐረር ከተማ ጀጎል ላይ የተከናወነውን ልማት በዋቢነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ተአምር ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሐረር ከተማ በተለይም በጀጎል የተሰራው ስራ ለልጆቻችን የአማረ ስፍራ መሻት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ያመላክታል፡፡ መስፋት እንዳለበት የሚታመን ሆኖ ጅምራችን ግን በጣም ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ብዙ ውጤቶች የታዩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአብነትም በቤት ላይ ቤት፤ በአጥር ላይ አጥር የነበረውን የኑሮ ዘይቤ ቀይረን ልጆች ወጣ ሲሉ የእግር ጉዞ የሚያደርጉበት እና ኳስ የሚጫወቱበት ከባቢን መፍጠር በጣም አስደሳች ጉይይ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

ጤናማ ከተማ እንዴት እንገንባ? (How to Build a Healthy City?) በተሰኘው የዊልያም ኤች መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የከተማ ፕላን እና የህዝብ ጤና የጠበቀ ትስስር ያላቸው በመሆኑ በኮሪደር ልማትም ሆነ መሰል የከተሞች እንቅስቃሴ ውስጥ በዋናነት ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡ ይህም አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድ ምቹ የሆኑ ከተሞችን መገንባት የሚያስችል ስለመሆኑም በመፅሐፉ ተመላክቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ ልማት ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እየተከናወነ ያለው ተግባር ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ነው፡፡ በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመስራት ባለፈ አዳጊዎች እግር ኳስ የሚጫወቱባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች የተሰሩበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች ከሚሰራው የኮሪደር ልማት ባሻገር የገጠር ኮሪደር ልማት መጀመሩን ጠቅሰው፣ ይህም ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ይገባቸዋል በሚል የተጀመረ ነው፡፡ የተሟላ ብልጽግናን የምናረጋግጠውም በዚሁ መንገድ ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

እንደባህር ዳር፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ ሐረር እና ሐዋሳ ያሉ ሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ተግባራዊ ሆኖ ከፍ ባለ ጥራትና ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኮሪደር ልማት ውጤታማነት ምን ያህል ለሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ጉልበትና ተስፋ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል የከተማ ልማት ባለሙያና የግል አማካሪ ኢንጅኒየር ታደሰ ተቋመ፡፡

በዓለማችን ለመጪው ትውልድ የተሻሉ ከተሞችን ለመፍጠር የኮሪደር ልማትን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ከተሞች አሉ። ለአብነትም  ኮፐንሃገን፣ ሲንጋፖር፣ ኦሪገንን የመሳሰሉ ከተሞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ የተጀመረው እና ወደሌሎችም ከተሞች ሰፍቶ ለውጥ እያስመዘገበ ያለው የኮሪደር ልማት ተተኪው ትውልድ ከበፊቱ የበለጠ ጥራት ያለው ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review