በፈረንጆቹ 2016 በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን የአውሮፓ ሀጋራት ለመከላከያ በቂ ወጪ ባለማድረጋቸው የአሜሪካ ግብር ከፋዮችን መጠቀሚያ አድርገዋል በሚል ወቅሰው ነበር።
በትናንትናው ዕለት በብራሰልስ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩት፣ ያለፈውን ውጥረት ለማስወገድ 5 በመቶ የሚሆነውን የኔቶ አባል ሀገራት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ለመከላከያ እንዲያወጡ ሀሳብ አቅርበዋል።
ከእጥፍ በላይ የሆነው ጭማሪው ከዚህ ቀደም 2 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ለመከላከያ ያውሉ ለነበሩት የአውሮፓ ሀገራት ከባድ ጥያቄ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል።
ዋና ፀሐፊው 3.5 በመቶው በቀጥታ ለመከላከያ ወጪ እንዲውል እና 1.5 በመቶው ደግሞ ከመከላከያ ጋር ተያያዥ ለሆኑ እንደ ኢንዱስትሪ ላሉ መሠረተ ልማቶች ሊውል እንደሚችል ጠቁመዋል።
አሜሪካ ቀድሞውኑ 3.4 በመቶ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷን ለመከላከያ የምታወጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለውጡ ከሌሎቹ ሀገራት አንፃር ብዙም እንደማይጎዳት ተነግሯል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግዝ፣ ብዙ ሀገራት በእቅዱ መስማማታቸውን ተናግረዋል።
5 በመቶ ለመድረስ ቀነ ገደብ ያልተቀመጠ ሲሆን፣ በ10 ዓመት ውስጥ ሀገራቱ ቀስ በቀስ ግቡን ያሳካሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከግቡ ላልደረሱ ሀገራት የተቀመጠ የቅጣት እርምጃ ባይኖርም፣ የደረሱበትን መሻሻል ለማወቅ ዓመታዊ እቅዶቻቸውን ማስገባት እንደሚጠበቅባችው ማርክ ሩት አስታውቀዋል።
በሊያት ካሳሁን