AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም
የንብረት ማስመለስ አዋጅ ማንኛውም ዜጋ ከህገወጥ ድርጊት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘት እንዳይችል የተጠያቂነት አሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ በ14ኛ መደበኛ ስብሰባው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ከህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አዳምጧል።
በምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ረቂቅ አዋጁ የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረትና ገንዘብ ለመያዝ፣ ለማገድና ለመውረስ የሚያስችሉ ግልጽ ድንጋጌዎችን መያዙን አብራርተዋል።
ማንኛውም ሰው ከወንጀል ድርጊት ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳያገኝ የሚያስችል አሰራር የሚዘረጋ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ግለሰብ የገባን የመንግስትና የህዝብ ንብረት በዘመድ አዝማድ ስም እንዳይደበቅ የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመሰረቱ ለመፍታት የህግ ክፍተቶችን መሙላት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የረቂቅ አዋጁ ተፈፃሚነት ላይ ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ ማንም ሰው በህጋዊ መንገድ ንብረት እንዲያፈራ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በህገወጥ ድርጊት የተገኘን ሀብት ማስመለስ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይሁንና አፈፃፀሙ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ረቂቅ አዋጁ አስር ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ ተፈፃሚ መሆኑ ከሌሎች ህጎች ጋር ምን ያህል ይጣጣማል የሚል ጥያቄም ተነስቷል።
ረቂቅ አዋጁ ላልተገባ ዓላማ እንዳይውልና የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እንዳያተኩር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሀብት ከማፍራትና ከመውረስ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ክልከላ የማያስቀምጥና ከአስር ዓመት በፊት አስር ሚሊየን ብር የነበረው ሰው ሀብት ያፈራበትን ማስረጃ እንዲያቀርብ መጠየቁ የተጠያቂነት ስርዓትን ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ።
የንብረት ህጋዊነት ማስረጃ ያቀረበ ሰው ያለአግባብ ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ አለመኖሩንና ማንኛውም ዜጋ በላቡ ሀብት የማፍራት መብቱን የማይጋፋ መሆኑንም አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 አድረጎ በሶስት ተቃውሞ ፣በአራት ድምፅ ተዓቅቦ ፣ በአብላጫ ድምጽ ማፅደቁን ከተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡