የአርሰናልን እና የፓሪሰን ዠርመ ጨዋታ ውጤትን የሚወስኑ ጉዳዮች

You are currently viewing የአርሰናልን እና የፓሪሰን ዠርመ ጨዋታ ውጤትን የሚወስኑ ጉዳዮች

AMN-ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በአርሰናል እና በፓሪሰን ዠርመ መካከል ይደረጋል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በየሊጎቻቸው ጠንካራ ተፎካካሪዎች ቢሆኑም የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ አንስተው አያውቁም፡፡

ሁለቱም ክለቦች ዋንጫ የሚያነሱበት ዓመት ዘንድሮ እንዲሆን ጠንክረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ምኞታቸውን ለማሳካትም ለፍልሚያ ዝግጁ ናቸው፡፡

በዚህ ምክንያት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታቸው በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ዘአናሊስት ድረገፅም የዛሬውን ጨዋታ ውጤት የመወሰን አቅም ያላቸው አራት ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡

የቡካዮ ሳካ እና የኑኖ ሜንዴዝ ትንቅንቅ

ቡካዮ ሳካ የአርሰናል ትልቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች ነው፡፡ ይህንንም በሪያልማድሪዱ ጨዋታ አሳይቷል፡፡ በተለይ በመልሱ ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት ስቶ ብዙም ሳይሸበር ግብ ያስቆጠረበት መንገድ የተጫዋቹ እድገት ከፍታ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡ አርሰናል በእርሱ ላይ እንደሚተማመን ማሳያው የቡድኑ 40 በመቶ የማጥቃት ሂደት ሳካ ባለበት የቀኝ መስመር መሆኑ ነው።

ቡካዮ ሳካ በዛሬው ጨዋታ የሚፋጠጠው ከፓሪሰን ዠርመ የግራ መስመር ተከላካይ ኑኖ ሜንዴዝ ጋር ነው። ፖርቱጋላዊው ተከላካይ በሊቨርፑሉ ጨዋታ ሞሃመድ ሳላህን መፈናፈኛ ሲያሳጣ አይተነዋል። በአስቶንቪላው ጨዋታ ደግሞ ግብ አስቆጣሪ መሆኑንም አስመስክሯል። ሁለቱ የየቡድኖቻቸው ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል ማን የበላይ ይሆናል የሚለው በትልቁ ይጠበቃል።

ሊውስ ስኬሊ እና የፓሪሰን ዠርመ የቀኝ መስመር

እንግሊዛዊው ወጣት ሊውስ ስኬሊ የዘንድሮ ዓመት ክስተት ሆኗል። ሪያል ማድሪድን ሲያሸንፉ የነበረው ብቃት ከአይን ያውጣህ የሚያስብል ነው።

በዛሬው ጨዋታ ግን ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። ምክንያቱም የፓሪሰን ዠርመ ዋነኛው የማጥቃት መስመር በእርሱ በኩል ነው። ፒኤስጂ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከየትኛውም ክለብ በላቀ መልኩ በቀኝ መስመር 77 የግብ ዕድሎችን ፈጥሯል። ሊውስ ስኬሊ የዚህን መስመር ምንጭ ማድረቅ ይጠበቅበታል።

የቶማስ ፓርቴ በቅጣ አለመግባት

ፓሪሰን ዠርመ ጨዋታን ለመቆጣጠር በትልቁ የሚጠቀሙት አማካይ ክፍሉን ነው። የማይታመን ብቃት እያሳየ የሚገኘው ቪቲንሃ ፣ ጆአኦ ኔቬስ እና ፋብያን ሪውዝን የያዘው ክፍል የቡድኑ የልብ ምት መሆኑን ደጋግሞ አሳይቷል። በጨዋታ ቢያንስ 598 የተሳኩ ኳሶችን ለሚቀባበለው ፒኤስጂ ጠንካራ አማካይ ክፍል የሌለው ተጋጣሚ ካገኙ ይፈነጩበታል። ቶማስ ፓርቴ በተለይ በማድሪዱ ጨዋታ አርሰናል የበላይ ሆኖ እንዲገኝ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። በዛሬው ጨዋታ ግን በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም። አርሰናልም የአማካይ ክፍሉን ያለፓርቴ እንዴት ያዋቅራል የሚለውን ለማየት ያጓጓል።

ግብጠባቂዎቹ

አርሰናልም ይሁን ፓሪሰን ዠርመ እዚህ ለመድረሳቸው ምክንያት አንዱ የግብ ጠባቂዎቻቸው ብቃት ነው። ብዙዎች ሳያምኑበት ከብሬንትፎርድ ወደ አርሰናል የመጣው ዴቪድ ራያ አሁን ጥያቄ የሚያነሳበት ሰው ብዙም የለም። ስፔናዊው ግብጠባቂ በ11 የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ስድስት ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት። ከሙከራዎቹ ጥራት መነሻ 10.4 ግብ ሊቆጠርበት ይገባ ነበር። በዚህ ስሌት ዴቪድ ራያ 4.4 ወደ ግብነት የመቀየር አቅም ያላቸውን ዕድሎች አምክኗል ማለት ነው።

ጂያን ሉጂ ዶናሮማም ለፒኤስጂ አለኝታ መሆኑን በበርካታ አጋጣሚዎች አሳይቷል። ጣልያናዊው ግብጠባቂ በተለይ ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት የመለያ ምቶችን አድኖ ለቡድኑ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዛሬውስ ጨዋታ የትኛው ግብ ጠባቂ ቡድኑን ይታደጋል? ምሽት አራት ሰዓት በኤምሬትስ የሚጀምረው ጨዋታ መልስ ይሰጠናል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review