AMN – የካቲት 9/2017 ዓ.ም
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት በአስተዳደሩ በሚገኙ 12ቱም ወረዳዎች 3ኛ ዙር የሌማት ትሩፋት የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ዋና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሹጉጤ የንብ ክላስተር መጀመሩ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ የምርት ጥራትና አቅርቦት ከመጨመር አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለዉ ገልፀዋል፡፡
በከተማ ውስጥ የከተማ ግብርናን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም የሚለውን የተሳሳተ አመለከከት በመስበር በከተማ ግብርናዉ ዘርፍ አመርቂ ዉጤት ማምጣት ተችሏልም ብለዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይም በከተማ ግብርና ለተሰማሩ ነዋሪዎች የግብዓትና ሙያዊ ድጋፍ የመስጠቱን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በየቤቱ የተጀመረዉ የሌማት ትሩፋት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የከተማ ግብርና ንቅናቄ በ3ኛ ዙር ማስጀመሪያው 16 ሺህ ዶሮዎችና የዶሮ መኖ ከነ ኬጁ /የዶሮ ቤት/ ድጋፍ አንደተደረገ ገልፀዋል።
በልዩ ድጋፉ ለ2 ሺህ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች እና በቤተሰብ ቢዝነስ/family business/ ለተደራጁ 480 ነዋሪዎች በድምሩ ለ2 ሺህ 480 ነዋሪዎች የ16 ሺህ የቄብ ዶሮ፣ የ356 ኩንታል መኖ እና ለእያንዳንዳቸዉ የዶሮ ኬጅ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኡርጎ በንብ ማነብ ክላስተር በግልና በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ለገቡ 36 ነዋሪዎች የ165 የንብ ቀፎና የንብ መንጋ መስጠቱን እንዲሁም በጓሮ አትክል ወደ ስራ ለሚገቡ የዘር ድጋፍ መደረጉን መግለፃቸውን ከክፍለ ከተማው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።