
AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በባህል የሚያስተሳስረው የ2024 የአቴከር ሕዝቦች የባህል ፌስቲቫል “የጋራ ቅርሶችን በማክበር፣ ወደ ሰላም፣ ብልጽግና እና የባህል ህዳሴ ጎዳና ማምራት” በሚል መሪ ሀሳብ በኡጋንዳ በድምቀት ተከፍቷል።
በፌስቲቫሉ መክፈቻ የኡጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከባለቤታቸው ጋር እንዲሁም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጀሲካ አሉፖ ታድመዋል።
የአቴከር ሕዝቦች የበላይ ጠባቂ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ መስቀል ጫላና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ተወካይ አቶ አህመድ መሀመድ ከኢትዮጵያ ታድመዋል።
የመክፈቻ ፕሮግራሙ የኬኒያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የደቡብ ሱዳን የጤና ሚኒስትር፣ የተርኪዬ፣ የቻይና፣ የሩሲያ፣ የታንዛኒያ እና የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
በፌስቲባሉ የተካተቱ አቴከር ተናጋሪ ማኅበረሰቦች፦ ከኢትዮጵያ ኛንጋቶም፣ ቶፖታ እና ባሪ፣ ከደቡብ ሱዳን ቶሪት፣ ኢቴሶ፣ ቱርካና እና ማሳይ፣ ከኬንያ ኢቴሶ፣ ካሪሞጆንግ፣ ጂዬ፣ ዶዶት፣ ኩማም፣ ላንጊ እና ካክዋ፣ ከኡጋንዳና ከታንዛኒያም ቁጥራቸው የበዛ ማሳይ እና ሌሎችም በምስራቅ አፍሪካ በባህልና ቋንቋ የተሳሰሩ ማኅበረሰቦች ተሳትፈዋል።
የኡጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የአቴከር ሕዝቦች የበላይ ጠባቂ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የኡጋንዳ ኛያንጋቶም ግዛት የባህል መሪ ቴሶ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም ከመቶ ዓመታት በኋላ እንደገና ተገናኘን፤ ከመቶ ዓመታት በፊት የመጣነው ከሀገራችን ኢትዮጵያ ነው፤ ማለታቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአቴከር ሕዝቦች የባህል ፌስቲቫል ከተበታተኑ እና ከተለያዩ ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ ለማኅበረሰቡ እንደ ደማቅ ማስተሳሰሪያ የሚያገለግል ፌስቲቫል ነው።
ፌስቲቫሉ አንድነትን ለማጠናከርና ቀጠናዊ ልማትን ለማጎልበት በሚረዱ ሀሳቦች ላይ መግለጫ በማውጣት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

All reactions:
3333