የአንጋፋው ሻምፒዮና አበርክቶ

ዓመታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወን የአትሌቲክስ ውድድር ነው። ይህ ሻምፒዮና መካሄድ የጀመረው ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአህጉራዊ፣ በዓለም አቀፍና በኦሎምፒክ የውድድር መድረኮች በመሳተፍ ድል የተቀዳጁ፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግና አትሌቶች ተሳትፈው ያለፉበትና የሚሣተፉበት የውድድር መድረክ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል የቻሉ አትሌቶችን ማፍራት ዋነኛ ዓላማው ነው፡፡ በእስካሁኑ ቆይታውም አንጋፋዎቹን አትሌቶች እነ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠርን ጨምሮ አሁን በውድድር ላይ እስካሉት ወጣት አትሌቶች ድረስ በርካቶችን አፍርቷል ይላል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ።

ሁሉንም የአትሌቲክስ የውድድር ተግባራትን አካትቶና ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄደው ይህ ውድድር በሀገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድሮች ላይ እየተሳተፉ ያሉና ለአትሌቲክስም እድገት የጎላ ሚና የተጫወቱ ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማትና ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርጥ አትሌቶቻቸውን ይዘው የሚሳተፉበት መድረክ እንደሆነም በፌዴሬሽኑ ከቀናት በፊት በተሰጠ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዘንድሮ ዓመት መርሃ ግብር ከሚያዝያ 28 ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል። በነገው ዕለት ፍጻሜውን የሚያገኘው ሻምፒዮናው በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ በርካታ ታዋቂና አዳዲስ ወጣት አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር አድርገውበታል፡፡

እየተካሄደ ያለው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዋነኛ ዓላማ እ.ኤ.አ በመስከረም ወር 2025 በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲመዝኑ፣ ለአትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር፣ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በሽልማት ለማበረታታት መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ ላይ ተመላክቷል።

በሻምፒዮናው በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ኮርስ የወሰዱ 80 ዳኞች የሩጫ፣ ዝላይና ሌሎች ውድድሮችን  እየመሩ ሲሆን፣  536 ሴት እና 843 ወንድ በአጠቃላይ 1 ሺህ 379 አትሌቶች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ 31 ክለቦችና ተቋማት እንዲሁም ታዋቂ አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን ሻምፒዮናው ለአትሌቲክሱ ስኬት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ይህ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገት የሚያደርገው አበርክቶም ቀላል አይደለም በሚለው ሀሳብ ብዙዎች ይስማማሉ። አትሌቶች እርስ በእርስ እንዲወዳደሩ እና ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ እድል መስጠት፣ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲዘጋጁ ማድረግ እና የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡

ፌዴሬሽኑም ውድድሩን ሲያካሂድ ከሚጠበቁበት ኃላፊነቶች መካከል  የውድድሩን ቦታ፣ ጊዜ፣ የውድድር መርሃ ግብር እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ሎጂስቲክሶችን ማዘጋጀት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቀጣይነት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሀሳባቸውን እያጋሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል በአትሌቲክስ ስፖርት ጉዳዮች ላይ ተንታኝ የሆነው ገብረሚካኤል ተክላይ አንዱ ነው፤ እርሱም በቀጣይ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ሀሳቡን እንደሚከተለው አጋርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የበለጠ ተመልካች ለመሳብ የቀጥታ ስርጭት ጥራቱን ማሻሻል፣ ፌዴሬሽኑ ዘመናዊ የጊዜ አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን፣ የአፈጻጸም መለኪያ መሳሪያዎችን እና የቀጥታ ስርጭት መሠረተ ልማቶችን በመግዛት ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ከሁሉም አስፈላጊ መገልገያዎች ጋር (ለምሳሌ ዘመናዊ የሩጫ ትራኮች፣ የመዝለያ ስፍራዎች) መገንባት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።

እንደዚሁም የአትሌቶችን ደህንነት መጠበቅ እና አበረታች መድሐኒት (ዶፒንግ) እንዳይጠቀሙ የበለጠ መቆጣጠር አስፈላጊ ስለመሆኑም ይመክራል።

በዚህ ውድድር ላይ በአሰልጣኝነት እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎችም አትሌቶቻቸው በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከመርዳት በተጨማሪ፣ አትሌቶች የተሻለ ልምድ እንዲያገኙና በውድድሩ ያገኙትን ልምድ ለቀጣይ እንዲጠቀሙበት ማስቻል እና አትሌቶች የሩጫ ቴክኒካቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት እንዳለባቸው አክሎ ይመክራል።

ክለቦችና ክልሎች በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፈው ጥሩ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን በመመልመል ቡድናቸውን ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል ሲልም ያክላል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የተከናወነው ሻምፒዮና በካሜሮን በተካሄደው 23ኛው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በጋና አክራ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ውድድር እንዲሁም በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳታፊ አትሌቶችን ለመለየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

አሁን እየተካሄደ ያለው እና ነገ የሚጠናቀቀው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ለቶኪዮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ አትሌቶች የሚለዩበት እንደሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህን በመክፈቻው እንደገለፁት፣ የውድድሩ ዋና ዓላማ እ.ኤ.አ ከሴፕቴምበር 13 እስከ 21 ቀን 2025 በጃፓን፣ ቶኪዮ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች የሚለዩበት ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም በጥገና ምክንያት አገልግሎት በማቆሙ አትሌቶች ለከፍተኛ እንግልትና ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ሻምፒዮናውን ደረጃውን ባልጠበቀ መም ለማካሄድ መገደዳቸውን ተናግረዋል። አያይዘውም ለችግሮቹ ዘላቂነት ያለው እልባት ለመስጠት እየተሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡

ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ በጀመረው እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የውድድር ታሪክ አንጋፋ በሆነው የዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተለያዩ ክልሎች፣ ክለቦች እና ተቋማት የተውጣጡ አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በትራክ ውድድሮች ከ100 ሜትር  እስከ 10 ሺህ ሜትር፣ መሰናክል፣ ውርወራና ዝላይ እንደዚሁም የምርኩዝ ዝላይ የመሳሰሉ ውድድሮችም ተሳትፎ ከሚደረግባቸው የውድድር አይነቶች ውስጥ ናቸው፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review