AMN – የካቲት 27/2017 ዓ.ም
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ዋና የምግብ ሰብሎችን ለከፍተኛ አደጋ እንዳጋለጣቸው ጥናት አመላከተ፡፡
‘ኔቸር ፉድ’ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ አዲስ ጥናት እንዳመለከተው የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር ከዓለም አቀፉ የምግብ ምርት አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
በፊንላንድ የሚገኘው የአልቶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጥናታቸው ፣ ሙቀት እና ደረቃማ የአየር ንብረት በዓለም የሚገኙ 30 ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ መርምረዋል፡፡
በዚህም የሙቀት መጨመር ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የዓለም ምግብ ምንጭ የሆኑትን ሩዝ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ድንችና አኩሪ አተር ከመሳሰሉ ዋና ዋና ሰብሎች የሚገኘውን ምርት በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርጋል መባሉን አናዶሉ አስነብቧል።
ይህም የምግብ ዋስትና እንዲቀንስ እንዲሁም በቂ ካሎሪና ፕሮቲን ማግኘትን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡
በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አካባቢዎች ለምግብነት የሚውሉ የሥራ ሥር ሰብሎች እንዲሁም የጥራጥሬ ዝርያዎች ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ሳብያ የሚፈጠረው የሙቀት መጨመር የሰብል ምርቶችን የሚያጠቁ አዳዲስ ተባዮች ሊያስከትል እንደሚችል እና ይህ ደግሞ ሁኔታውን የበለጠ እንደሚያባብሰው ተመላክቷል፡፡
የዓለም ምግብ ስርዓትን ለመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን እና የሚያስከትላቸውን አደጋዎች መከላከል አስፈላጊ መሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡