የአዲስ አበባ ከተማ የ5 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ዕቅድ ይፋ ሆነ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ የ5 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ዕቅድ ይፋ ሆነ

AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በዛሬው ዕለት የ5ዓመት የትራፊክ ድህነት ስትራቴጂ ዕቅድ ይፋ አድርጓል።

ከ2025 እስከ 2030 ተግባራዊ የሚደረገው የመንገድ ትራፊክ ስትራቴጂ ዕቅድ በከተማዋ የሚታየውን ሞትን እና የአካል ጉዳትን በ25% የመቀነስ ግብ ያደረገ ነው ተብሏል።

ግቡን ለማሳካት እንዲቻል 7 ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የተለዩ መሆናቸውን የገለጸው የመንገድ ደህንነት አስተዳደር ስርዓትን መዘርጋት ፤የመንገድ ትራፊክ ግጭት በሚበዛባቸው ዋና መንገዶች ላይ ማተኮር ፤በግንዛቤ ማስጨበጥ የተደገፉ ቁልፍ የደህንነት ህጎችን መተግበር ፤የመንገድ ትራፊክ ግጭት እና ጉዳት መረጃ አስተዳደር ስርዓትን ማዘመን ፤የድህረ-አደጋ ምላሽ እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመር የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ እንደገለጹት የከተማዋን የትራንስፖርት ስርዓት አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ ተደራሽ፣ ምቹ፣ወቅቱ በደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ ፈጣንና ዘመናዊ እንዲሆን ለማስቻል ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን ተቋማት ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በላቀ ቅንጅትና በልዩ ትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን በመርሃ ግብሩም ላይ ገልጸዋል ።

የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በተጨባጭ ማረጋገጥ እንዲቻል ይፋ የተደረገውን ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ ካለው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ስራ ጋር በማጣጣም ሞተር አልባ የትራንስፖርት ስርዓትን ማስፋፋት ፣ፈጣንና ዘመናዊ የብዙሃን ትራንስፖርት አማራጮችን በሚፈለገው አግባብ ማስፋት ፤የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ለማረጋገጥ ከካርበን ልቀት በጸዳ መልኩ የግልና የብዙሃን የትራንስፖርት አማራጮችን ወደ ኤሌክትሪክ ማሸጋገርን ጨምሮ የትራንስፖርት ስርዓቱ በተሟላ መልኩ በቴክኖሎጂ የሚደገደገፍ እንዲሆን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በበኩላቸው በምክትል ከንቲባ የሚመራው፤ በ2009 ዓ.ም በከተማዋ የተቋቋመው የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት ለ13 ዓመታታ የሚዘልቅ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ከ2010 ዓ.ም አንስቶ በርካታ ተግባራትን ሲያከናወን መቆየቱ ይታወቃል ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው የተሻሻለው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለቀጣይ አምስት ተከታታይ ዓመታት ስራ ላይ የሚውል ነውም ብለዋል።

በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ዓመታት ልዩ ልዩ የመንገድ ደህንነት ስራዎችን በማከናወኑ ከ2010 ዓ.ም በፊት ለተከታታይ ዓመታት 6 በመቶ እንደጨመረ የዘለቀውን የትራፊክ አደጋ አሃዝ በነበረበት ካማስቆም ባሻገር ከ 5 በመቶ በታች መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

የትራፊክ ደህንነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ተግባር ብቻ ሳይሆን የመንገድ ተጠቃሚ የተሽከርካሪ ባለንብረቶችና የእግረኞችም ጭምር በመሆኑ ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ተብሏል።

በመርሃ ግብሩም ላይ ተግባራዊ የሚደረገውን የአምስት አመት ስትራቴጂ ዕቅድ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት መካሄዱን ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review