የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሻግሯል

You are currently viewing የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሻግሯል

AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ተግባራዊ የተደረጉ የወንዝ ዳር እና የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በሌሎች መሰረተ ልማቶች የታየው አስደማሚ ለውጥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን እያነቃቃ ይገኛል፡፡

በቅርቡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመውሰድ ጆሃንስበርግ ከተማን መቀየር እንደሚገባ በቁጭት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

አሁን ደግሞ የኬኒያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በ50 ቢሊየን የኬኒያ ሽልንግ (ከ386 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ) በሚሆን ወጪ በናይሮቢ የወንዝ ጥበቃ እና የወንዝ ዳር ልማት መርሀ-ግብር ትግበራን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩም፣ ናይሮቢ ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ፅዱ እና ደህንነቷ የተጠበቀ ከተማ እንድትሆን መንግስት አንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለህይወት ክብር የሚሰጥ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ዘላቂ የትራንስፖርት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ህይወት ቀያሪ ተነሳሽነት እንደሆነም ገልፀዋል።

በቀጣይ 24 ወራት ውስጥም በናይሮቢ የወንዝ ዳር ለውጥ የሚታይበት እንደሚሆን ለኬኒያ ህዝብ አረጋግጣለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በናይሮቢ የወንዞች ኮሚሽን እና በሌሎች ተቋማት ትብብር የሚተገበረው ፕሮጀክት 40 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል፡፡

የናይሮቢ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ እና በኢኮኖሚ የላቀች የሚያደርጋት እንደሆነና የዜጎችን አቅም ያገናዘበ የቤቶች ግንባታ፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን አጣምሮ መያዙንም ማመላከታቸውን ኬ ዲ አር ቲ ቪ ዘግቧል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review