AMN – መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነቡ እና ወደ አገልግሎት የገቡ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን በተሳተፉበት በዚሁ ጉብኝት የአዲስ አለም ዓቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን፣ የገላን ጉራ የልማት ተነሺዎች የጋራ መኖሪያ መንደርን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ በራስ አቅም የተገነባ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ጉብኝት ላይ የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ ፣ ማዕከሉ በ40 ሄክታር ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቅሰው በውስጡ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቶች የሚሰጡበት እንደሆነ አስረድተዋል።
ማዕከሉ ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ አዲስ አበባ ከፍታዋን የሚጨምር እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ጉባኤዎችና ኤግዚቢሽኖችን ማስተናገድ የሚያስችል እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናታለም መለሰ ናቸው።
የለሚ አደባባይ በአካባቢው የተገነባ ሌላኛው የከተማዋ ውበት መሆኑን የተናገሩት የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ከመስቀል አደባባይ ቀጥሎ በትልቅነቱ ሁለተኛው የሕዝብ አደባባይ ነው ብለዋል።
በምትኩ ተሾመ