የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 4ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት በአድዋ መታሰቢያ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በስብሰባዉ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ የሚገኙ ሲሆን መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተለያዩ ሪፎርሞችን እየተገበረ መሆኑን ይህም ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል በተሰራው ስራ ለሸማቹ የማህበረሰብ ክፍል የግብርናና መሰል ምርቶችን ከማቅረብና ከመደጎም ረገድ ሊበረታቱ የሚገባቸዉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን ሪፎርሙን በአግባቡ ያልተገነዘቡ አንዳንድ ነጋዴዎች ምርቶችን በተለጠፈው ዋጋ እንደማይሸጡ በተለይ ከዘይት ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አንስተዋል፡፡
በምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
በቅዳሜና እሁድ የግብይት ማእከላት ለሸማቾች የሚቀርቡ ምርቶች ሌላው ነጋዴ ከሚሸጥበት ዋጋ እምብዛም ልዩነት የለውም ይህም ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በህብረት ስራ ማህበራት ዘርፍ የተጀመረው ሪፎርም ሊጠናከር ይገባል የማህበራት አቅምም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡