በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ዙሪያ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች፣ በደላሎች እና በማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ዙሪያ የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በተሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጥ መመጣቱን በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ይህንን አሰራር ለማዘመንና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ግብርናን በተለይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን ከተለምዶ (ከወረቀት) አሰራር ወደ ዲጂታል ማሸጋገር ወቅታዊና የመንግስት የትኩረተ አቅጣጫ መሆኑንና ይህንን ስራ የሚያግዝ ሶፍትዌርም እየበለጸገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ይህ እየለማ የሚገኝው ሶፍትዌር የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት በመሬቱ ልክና በሰብል ዓይነት መሆኑን ከማረጋገጡም ባሻገር በስርጭት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በተሳካ ሁኔታ ሙከራ እየተደረገ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።