“ኢትዮጵያውያን ታላቅ ህዝቦች ናቸው። ለአፍሪካውያን ነፃነት በጀግንነት የተዋደቁ፣ አፍሪካውያን ነፃነታቸውና መብታቸው እንዲጠበቅ፣ የራሳቸውን ዕጣ ፈንታና የውስጥ ጉዳያቸውን ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ቁጥጥር ሙሉ ሉዓላዊነታቸው ተጠብቆ መወሰን እንዲችሉ የደከመ ህዝብ ነው፡፡”
ይህ የመጀመሪያው የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት እና መሪ የነበሩት አህመድ ሴኩ ቱሬ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የመጀመሪያ ጉባኤ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1963 በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው፡፡ አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች ቀንበር ስር ሆና ትዳክር በነበረበት 19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቁጥጥር ስር ልታውላት የመጣችውን ጣሊያንን በዓድዋ ጦርነት ድል በማድረግ ነፃነቷን አስጠብቃ መቀጠል ቻለች፡፡የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካውያን፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁርና ጭቁን ህዝቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። አውሮፓውያን በጥቁር ህዝብ ላይ የበላይ ተደርገው እንዲሳሉ ያደረገውን አፈ ታሪክ እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡
የዓድዋ ድልን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት አደገ። በዚህም የዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል መሆን ችላለች፡፡ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ጥረት ብታደርግም የተሳካ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን እንዲያገኙ በዓለም አቀፍ መድረኮች በመሟገት፣ የስልጠና፣ ቁሳቁስ፣ የዲፕሎማሲና ሞራል ድጋፍ አድርጋለች፡፡ በዚህም የተነሳ በአፍሪካውያን ዘንድ ልዩ ክብርና ቦታ አላት።
አቶ መኮንን ከተማ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ ናቸው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት አስተዳደር ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመስረት ትልቅ ሚና የተጫወቱት የአቶ ከተማ ይፍሩ ልጅ ናቸው፡፡ “ከተማ ይፍሩ፤ የሰላም፣ የእድገትና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ” በሚል ርዕስ የአባታቸውን ታሪክና አበርክቶ የያዘ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ የትናንቱን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬውን የአፍሪካ ህብረት ከጥንስሱ ጀምሮ በሁለት እግሩ እንዲቆም በማስቻል የመሪነት ሚናዋን መጫወቷን ያነሳሉ፡፡
አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ “እንዴት አንድነት እናምጣ?” በሚለው ሀሳብ ላይ በሁለት ቡድን ተከፋፍለው ነበር፡፡ “ፖለቲካዊ ውህደት በማድረግ አንድ አፍሪካን እንፍጠር” የሚሉት እንደ ጋና፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ሞሮኮ ያሉ አገራትን ያቀፈው የካዛብላንካ ቡድን እና “በኢኮኖሚ ከተሳሰርን በኋላ ነው ወደ ውህደት ማምራት ያለብን” የሚሉ እንደ ላይቤሪያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ አይቮሪኮስት ያሉ የሞኖሮቪያ ቡድን አባል አገራት መካከል አለመግባባት ብሎም ንግግር እስከማቆም የደረሰ ልዩነት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ “አፍሪካ ተከፋፍላ መቆየት የለባትም” በሚል ሁለቱንም ቡድኖች በተናጠል በማነጋገርና በማግባባት እንዲቀራረቡና ወደ አንድ እንዲመጡ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ እንዲመሰረት አድርጋለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዲሆን መደረጉ አንደኛው ምክንያት ይህ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ መነሳሳት በመፍጠር፣ በተለያየ መልኩ በመደገፍ፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላም ወደ አንድነት እንዲመጡ ባደረገችው ታላቅ ውለታ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያና የልብ ትርታ መሆን ችላለች። የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት፣ የተለያዩ አህጉራዊና ቀጣናዊ ድርጅቶች መቀመጫ እንዲሁም በርካታ ኤምባሲዎችና ቆንሲላዎች የሚገኙበት ከተማ ልትሆን ችላለች፡፡ ለዚህም ተከታታይ ትውልዶች ጥበብ የተሞላበት የዲፕሎማሲ ትግል አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ መዲናነትን የማጽናት ስራ
የአፍሪካ ህብረት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ህብረቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚያካሂዳቸው ጉባኤዎች መካከልም አንደኛውን በየዓመቱ ታስተናግዳለች፡፡ በርካታ ዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ጉባኤዎች ይካሄዱባታል፡፡
አዲስ አበባ አፍሪካውያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚቆጥሯት፣ የሚሰባሰቡባት፣ የአህጉሪቱን እጣ ፈንታና ጉዞ የሚወስኑ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩባት፣ የሚወስኑባትና በርካቶችም የሚኖሩባት ከተማ ናት፡፡ እንደ አፍሪካ መዲናነቷ የአፍሪካ ታሪክ፣ ማንነትና ባህል የሚንፀባረቅባት፣ አፍሪካውያን የሚዝናኑባት፣ የሚጎበኟትና የሚኖሩባት ለኑሮ ምቹና ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትላልቅ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ረገድ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ማንሳት ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ፣ ነፃነትና አንድነት ስናነሳ የዓድዋ ድልን አለማንሳት አይቻልም፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ተይዘው በሚማቅቁበት ወቅት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሊገዛት የመጣውን ጣሊያንን ድል ያደረገችበት የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ከቅኝ ግዛት የመውጣት ትግል ውስጥ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ ለድሉም ምልክት የሚሆን ሙዚየም፣ ትላልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሲኒማ ቤት፣ የፓን አፍሪካኒዝምና ሌሎችን አካትቶ የያዘ ግዙፍና ማራኪ መታሰቢያ በአፍሪካውያን መዲና እንዲቆም ተደርጓል፡፡
የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪው አቶ ከተማ እንደሚሉት፤ መታሰቢያው መገንባቱ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ድሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች ድል ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩ ሀገሮች “እኛም እንችላለን” ብለው ለነፃነታቸው እንዲታገሉ መነሳሳት የፈጠረ፣ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የተሰራ ነው፡፡ ዛሬ ላይ መታሰቢያው ወደ መዲናዋ ለተለያዩ ኮንፈረንሶች የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎችና አፍሪካዊያን የሚጎበኙትና ከታሪካቸው ጋር የሚገናኙበት ቦታ ሆኗል፡፡
ሌላው እድሳት ሲደረግለት ቆይቶ በዘንድሮ ዓመት በጥቅምት ወር የተመረቀው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ የሚገኘው ታሪካዊው የአፍሪካ አዳራሽ አዲስ አበባ በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያላትን ስፍራ ከፍ ያደረገ ነው፡፡ አዳራሹን በአፍሪካ ታሪክ ልዩ ምዕራፍ እንዲኖረው ያደረገው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት በጊዜው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የድርጅቱን መመስረቻ ስምምነት (ቻርተር) የተፈራረሙበት መሆኑ ነው፡፡ እድሳቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመደበው 57 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ የተከናወነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በዓይነት መልክ ለቋሚ ኤግዚቢሽን ማሳያ ግንባታና ኤግዚቢሽኑን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ የሚሆን 3 ሺህ 100 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቷል፡፡

የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው አቶ መኮንን እንደሚሉት የአፍሪካ አዳራሽ በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው ስፍራ እንደመሆኑ መታደሱ “ታሪካችንን እያከበርነው መሆኑን ያሳያል፡፡ እኛ ታሪካችንን ስናከብር፣ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ያከብሩናል፡፡ አፍሪካውያን ወንድምና እህቶቻችን በመሰብሰብ እንደ አንድ ቤተሰብ የተቀመጥንበት፣ አፍሪካን አንድ ለማድረግና ወደፊት እንድትጓዝ የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች ውይይት ያደረጉበት ቦታ ነው፡፡” ሲሉ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች የአዲስ አበባን የአፍሪካ መዲናነት አስጠብቆ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
እንደ እንጦጦ፣ አንድነት፣ ወዳጅነት አደባባይ ያሉ ትላልቅ ፓርኮች መገንባት፣ በኮሪደር ልማት የከተማዋን የመንገድ፣ የፍሳሽና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች የማዘመን፣ የወንዝ ዳርቻዎችን የማልማት፣ ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ፣ የመዝናኛና ለኑሮ የምትመች ከተማ እንድትሆን የሚሰሩ ስራዎችም አዲስ አበባ እንደ አፍሪካ መዲናነቷ በሚመጥናት ደረጃ ልክ እንድትገኝ ያስችላሉ፡፡
አዲስ አበባ ስትዋብ፣ ስትፀዳና የምትሰጠው አገልግሎት ሲዘምን የአዲስ አበባ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን መዲናዋን እንደ ቤታቸው የሚቆጥሯት አፍሪካውያንንም ደስ ያሰኛል። ምክንያቱም አፍሪካውያን ኢትዮጵያን በጣም ይወዳሉ፡፡ በዓድዋ ድል የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግልን በማቀጣጠል፣ አፍሪካውያን ወደ አንድነት እንዲመጡ በማስተባበር የተጫወተችውን ሚና በደንብ ይገነዘባሉ፤ ይላሉ አቶ ከተማ፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የኮሪደር ልማት፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን እና ኤግዚቢሽን ሴንተር ግንባታን ተዘዋውረው የጎበኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶችም፣ የልማት ስራዎቹ የአዲስ አበባን ደረጃ ከፍ ያደረጉና ገፅታ የቀየሩ መሆናቸውን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰሜን አሜሪካ ዳይሬክቶሬት ባልደረባ ዮሐንስ ገበየሁ እንዳሉት፣ “በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገራችንን የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ በማገዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል። አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን፣ የተለያዩ ኮንፈረንሶች መምጣት እንዲችሉና በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ የሚያደርጋት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በታሪክ የነበረንን ሚና በሚጨበጥና በሚታይ ነገር የምናስቀጥልበት ሌላኛው መንገድ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ይህን ሀሳብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመንግስት ኮንፈረንስ ዝግጅትና ፕሮቶኮል ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ለገሰ ይጋሩታል፡፡ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለመሳብ በአዲስ አበባ ትልቁ ችግር የነበረው የተደራጀና በቂ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አለመኖር ነበር፡፡ በርካታ ኮንፈረንሶችም በተለያዩ አገሮች ይካሄዱ ነበር፡፡ የአዲስኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ሴንተር በማድረግ በርካታ የኮንፈረንስ አዳራሾች እንዲኖሩ በማስቻል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በከተማዋ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአፍሪካ ታሪክ፣ ስልጣኔና ባህል እንዲሁም በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጭምር ያስተማሩት የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሬ (ፕ/ር) ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንዳጋሩት፣ አፍሪካውያን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽን ብቻ አይተው አይመለሱም። የህዝብ መናፈሻና ፓርኮች እንዲሁም የባህል ማዕከላትን እየጎበኙ የሚዝናኑበትና የሚማሩበትን ዕድል ይፈጥራል። ለምሳሌ፡- የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከኢትዮጵያ ባለፈ አፍሪካውያንን የሚያሳትፍ ኹነት ለማዘጋጀት ይጠቅማል፡፡
ቀጣይ ምን ይጠበቃል?
አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና ብቻ ሳትሆን በዓለም ላይ ከኒውዮርክና ጄኔቭ በመቀጠል ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ ናት። ከተማዋ የአፍሪካውያን መዲናነቷን አስጠብቃ ለማስቀጠል አሁንም በተለያየ መልኩ መስራት እንደሚገባት የአፍሪካ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ለምሳሌ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ህብረት) የተመሰረተበት ግንቦት 17 ቀን በየዓመቱ “የአፍሪካ ቀን” ተብሎ ይከበራል። ይህንን በዓል መንግስትን ጨምሮ በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት በዓል ማድረግ ቢቻል፣ ለአፍሪካውያን ወንድም እና እህት ህዝቦች የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ይሆናል፤ ይላሉ የአፍሪካ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ መኮንን ከተማ፡፡
ሌላው አፍሪካን ወደ አንድነት የማምጣት ጉዞ ተጀምሮ ያላለቀ ነው፡፡ ባለንበት ዘመን አንድ ሀገር ብቻውን በተናጠል በመሄድ የትም መድረስ አይችልም፡፡ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን መቅረፍና ማደግ የሚችሉት በኢኮኖሚ፣ በሰላምና በሌሎችም መስኮች እርስ በርስ መተሳሰርና መተጋገዝ ሲችሉ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መወጣት እንደሚገባት ያስገነዝባሉ፡፡
አዲስ አበባ እንደ አፍሪካ መዲናነቷ ከጊዜው ጋር እየዘመነች መሄድ እንደሚጠበቅባትም አቶ መኮንን ያነሳሉ፡፡ ያኔ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት የት ይሁን? ሲባል፤ ናይጄሪያ “ትልቅና የተሻለ ከተማ አለኝ” በሚል እድሉ እንዲሰጣት ጠይቃ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ነፃነት ያበረከተችው ሚና ከግምት ውስጥ ገብቶ አዲስ አበባ መቀመጫ እንድትሆን ተደርጋለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ህብረቱ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ቅስቀሳዎች ይደረጋሉ፡፡ ይህንን ለማስቆም መዲናዋን በሚመጥናት ልክ እንድትገኝ መስራት፤ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነፃነት ትግል የተጫወተችውን ሚና ማሳወቅ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
ከተማዋ በታሪክ በአፍሪካውያን ነፃነትና አንድነት ታሪክ ያላትን ስፍራ፣ የታሪክና ሌሎች ካፒታሎች ወደ ኢኮኖሚ እና ባህል መቀየር፣ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መኖሪያ መሆኗን የሚያመላክቱ ማሳያዎች የሚታዩባት ከተማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሰረተ ልማት፣ በኢንፎርሜሸን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ሌሎች መስኮች የከተማ አስተዳደሩ፣ የፌዴራል መንግስት እና ሌሎች ተቋማትን አስተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ፣ የአፍሪካውያን መናኸሪያ መሆኗ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች አሉት፡፡ በቅርብ ዓመታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም የመዲናዋን የአፍሪካ ዋና ከተማነት የምትመጥን ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎችም የአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችላት ነው፡፡ ዓለም የፉክክር መድረክ እንደመሆኗ ከተማዋ በመሰረተ ልማት፣ በአገልግሎት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ተወዳዳሪ፣ ለጎብኚዎችና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ፣ አፍሪካዊ ገፅታን የማላበስ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ