AMN- የካቲት 7/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የአልጄሪያ ፕሬዝደንት እና የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ሰብሳቢ አበዱልመጅድ ተቡን ገለጹ።
የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት የአፍሪካ አገራት አጀንዳ 2063ን ከማስፈጸም አንጻር በኢኮኖሚ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያከናወኑት ስራ የሚገመገምበት መድረክ ነው።
የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት 3ኛ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ እና 34ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።ስርአቱ በመድረኩ የተገመገሙ አገራትን ሪፖርት አድምጦ አጽድቋል።
እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ለመገምገም ያመለከቱ አገራትን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን በተጨማሪም የአቻ መገማገሚያ ስርአት መድረኩን የአንድ አመት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አጽድቋል።
የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ሰብሳቢ አብዱልመጅድ ተቡን በዚሁ ወቅት ስርአቱ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት አስፈላጊ መሳሪያ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር ጠቃሚ ዘዴ እንደሆነ በማስታወቅ አባል ሀገራት በፈቃደኝነት ለዚህ ስርአት መዋጮ በመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ስኬት የሚጀምረው ከ20 ዓመታት በፊት ከተደረሰው ስምምነት አንስቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአቻ ግምገማው የመሳተፍ የአገራት ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣቱንና ተቋማዊ መሆኑን በመጥቀስ ስርአቱ በፈቃደኝነት ለሚገመገሙ አገራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት በአህጉሪቱ የመንግስት አስተዳደርን ለማሻሻል ወሳኝ መሣሪያ ነው ያሉት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ናቸው።
በአህጉሪቱ ሰላም፣ ብልጽግና እና ውህደትን ለመፍጠር ወሳኝ ዘዴ መሆኑን ገልጸው የአጀንዳ 2063 ራእይን ለማስፈጸም ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።