የአፍሪካን የመልማት አቅም ወደ ውጤት የምንቀይርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN ግንቦት 12/2017 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዘላቂ የግብርና ልማዶችን፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ለአርሶ አደሮች የገበያ ተደራሽነትን በማጠናከር የአፍሪካን የመልማት አቅም ወደ ውጤት የምንቀይርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልዋል።

በሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብራዚል ገብተዋል።

‎ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ሰፊ ፋይዳ ባለው ጉባዔ ተሳትፎ ጎን ለጎን ከብራዚል ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም ከኢንዱስትሪና ልማት ሚኒስትር ጀራልዶ ሮድርጌዝ አልካሚን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አከናውነዋል።

‎በውይይቱ ወቅት የብራዚል ምክትል ፕሬዝደንቱ የኢትዮጵያን ፈጣን እድገትና በጥሩ መሰረት ላይ የሚገኘውን የሀገር ውስጥ ምርት መነቃቃትን ያደነቁ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት በትብብር እየተገበሯቸው ከሚገኙ ስራዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ጠንካራና ዘመናዊ የአቬሽን ዘርፍ ሀገራቸው አብሮ የመስራት ሰፊ ፍላጎት እንዳላትም ጠቅሰዋል።

‌‎ኢትዮጵያ እና ብራዚል ከዚህ ቀደም በግብርና፣ የደን ልማት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም የአሲዳማ አፈር አጠቃቀም ፕሮጀክቶችን በትብብር የመስራት ስምምነት እንደነበራቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በውይይታቸውም ስትራቴጂያዊ ትብብሮችን በተለይም በግብርና፣ ዘላቂ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ ተቀራበው ለመስራት የሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንዳደረጉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review